የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 71:1-16

መዝሙር 71:1-16 NASV

እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መጠጊያ አደረግሁ፤ ከቶም አልፈር። በጽድቅህም ታደገኝ፤ አስጥለኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ አድነኝም። ምን ጊዜም የምሸሽበት፣ መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤ አንተ ዐለቴ ምሽጌ ነህና፣ ታድነኝ ዘንድ ትእዛዝህ ይውጣ። አምላኬ ሆይ፤ ከክፉ እጅ፣ ከግፈኛና ከጨካኝ መዳፍ አውጣኝ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ተስፋዬ፣ ከልጅነቴም ጀምሮ መታመኛዬ ነህና። ከተወለድሁ ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፤ ከእናቴ ማሕፀን ያወጣኸኝ አንተ ነህ፤ አንተ የዘወትር ምስጋናዬ ነህ። ብዙዎች እንደ ትንግርት አዩኝ፤ አንተ ግን ጽኑ ዐምባዬ ነህ። ቀኑን ሙሉ ክብርህን ያወራ ዘንድ፣ አፌ በምስጋናህ ተሞልቷል። በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጕልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ። ጠላቶቼ ተነጋግረውብኛልና፣ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ በአንድ ላይ አሢረዋል፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያስጥለው የለምና፣ ተከታትላችሁ ያዙት” አሉ። አምላክ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ባላንጣ የሆኑብኝ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤ ሊጐዱኝ የሚፈልጉ፣ ንቀትንና ውርደትን ይከናነቡ። እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል፤ ማቆሚያ ልኩንም አላውቅም። መጥቼ የጌታ እግዚአብሔርን ብርቱ ሥራ ዐውጃለሁ፤ የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ።