መዝሙር 71:1-16
መዝሙር 71:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጠው፥ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥ ሕዝብህን በጽድቅ፥ ድሆችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ። ተራሮችና ኮረብቶች የሕዝብህን ሰላም ይቀበሉ። ለድሆች ሕዝብህ በጽድቅ ፍረድ፥ የድሆችንም ልጆች አድናቸው። ትዕቢተኛውንም አዋርደው። ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥ በጨረቃም ፊት ለልጅ ልጅ ይኑር። እንደ ጠል በባዘቶ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይወርዳል። በዘመኑም ጽድቅ ይበቅላል፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ይገዛል። በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈርን ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ፤ የምድር ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል ፥ አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል። ድሃውን ከሚቀማው እጅ፥ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለድሃና ለምስኪን ይራራል፥ የድሆችንም ነፍስ ያድናል። ከአራጣና ከቅሚያ ነፍሳቸውን ያድናታል፤ ስሙም በፊታቸው ክቡር ነው። እርሱ ይኖራል፥ ከዓረብም ወርቅን ይሰጡታል፤ ሁልጊዜም ስለ እርሱ ይጸልያሉ፥ ዘወትርም ይመርቁታል። በተራሮች ራስ ላይ ለምድር ሁሉ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ዛፍ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።
መዝሙር 71:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መጠጊያ አደረግሁ፤ ከቶም አልፈር። በጽድቅህም ታደገኝ፤ አስጥለኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ አድነኝም። ምን ጊዜም የምሸሽበት፣ መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤ አንተ ዐለቴ ምሽጌ ነህና፣ ታድነኝ ዘንድ ትእዛዝህ ይውጣ። አምላኬ ሆይ፤ ከክፉ እጅ፣ ከግፈኛና ከጨካኝ መዳፍ አውጣኝ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ተስፋዬ፣ ከልጅነቴም ጀምሮ መታመኛዬ ነህና። ከተወለድሁ ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፤ ከእናቴ ማሕፀን ያወጣኸኝ አንተ ነህ፤ አንተ የዘወትር ምስጋናዬ ነህ። ብዙዎች እንደ ትንግርት አዩኝ፤ አንተ ግን ጽኑ ዐምባዬ ነህ። ቀኑን ሙሉ ክብርህን ያወራ ዘንድ፣ አፌ በምስጋናህ ተሞልቷል። በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጕልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ። ጠላቶቼ ተነጋግረውብኛልና፣ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ በአንድ ላይ አሢረዋል፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያስጥለው የለምና፣ ተከታትላችሁ ያዙት” አሉ። አምላክ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ባላንጣ የሆኑብኝ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤ ሊጐዱኝ የሚፈልጉ፣ ንቀትንና ውርደትን ይከናነቡ። እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል፤ ማቆሚያ ልኩንም አላውቅም። መጥቼ የጌታ እግዚአብሔርን ብርቱ ሥራ ዐውጃለሁ፤ የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ።
መዝሙር 71:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! እንድትጠብቀኝ ወደ አንተ ስለ መጣሁ ኀፍረት እንዲደርስብኝ አታድርግ! በጽድቅህ ከችግር እንዳመልጥ አድርገህ አውጣኝ አድምጠህም አድነኝ። በምሄድበት ቦታ ሁልጊዜ አንተ ኀያል አምባዬ ሁን፤ አንተ ኀያል አምባዬና ምሽጌ ስለ ሆንክ በትእዛዝህ አድነኝ። አምላኬ ሆይ! ከክፉ ኀይልና ርኅራኄ ከሌለው ዐመፀኛ እጅ አድነኝ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ተስፋዬን በአንተ ላይ አደርጋለሁ፤ ከልጅነቴ ጀምሮ መታመኛዬ አንተ ነህ። በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በአንተ ላይ እታመናለሁ፤ ከእናቴ ማሕፀን እንድወለድ ያደረግኸኝ አንተ ነህ፤ እኔም ዘወትር አመሰግንሃለሁ። አንተ ብርቱ ተከላካይ ስለ ሆንክልኝ ሕይወቴ ለብዙዎች ምሳሌ ሆኖአል። አንደበቴ በአንተ ምስጋና የተሞላ ነው፤ ስለ ክብርህም ቀኑን ሙሉ እናገራለሁ። ድምፄንም ከፍ አድርጌ ለአንተ ምስጋና አቀርባለሁ። አሁንም በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ደካማ በምሆንበትም ጊዜ አትተወኝ። ጠላቶቼ በእኔ ላይ ክፉ ነገር ይመክራሉ፤ ሊገድሉኝ የሚፈልጉትም በእኔ ላይ ያሤራሉ። “እግዚአብሔር ትቶታል፤ ተከታትለን እንያዘው፤ የሚያድነው ማንም የለም” ይላሉ። አምላክ ሆይ! ከእኔ አትራቅ፤ አምላክ ሆይ! ፈጥነህ እርዳኝ። ተቃዋሚዎቼ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤ ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ይናቁ፤ ይዋረዱም። እኔ ግን ዘወትር አንተን ተስፋ አደርጋለሁ፤ በበለጠም መላልሼ አመሰግንሃለሁ። ምንም እንኳ ማስተዋል ቢያዳግተኝ፥ አንደበቴ ስለ ትክክለኛ ፍርድህና ስለ አዳኝነትህ ቀኑን ሙሉ ይናገራል። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! መጥቼ ኀያል ሥራዎችህን ዐውጃለሁ፤ ትክክለኛ ፍርድ የመስጠት ኀይል የአንተ ብቻ መሆኑን እናገራለሁ፤
መዝሙር 71:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፥ ለዘለዓለም አልፈር። በጽድቅህ አስጥለኝ ታደገኝም፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም። ሁልጊዜ የምጠጋበት ዓለት ሁነኝ፥ ጠንካራ መሸሸጊያ፥ ዓለቴና መጠጊያዬ አንተ ነህና። አምላኬ፥ ከክፉ እጅ፥ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ። አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ አቤቱ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና። ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው። ለብዙዎች መደነቂያ ሆንሁ፥ አንተ ግን ብርቱ መጠጊያዬ ነህ። አፌን ምስጋና ሞላ ሁልጊዜ ክብርህንና እዘምር ዘንድ። በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ። ጠላቶቹ በላዬ ተናግረዋልና፥ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ፦ “እግዚአብሔር ትቶታል፥ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት።” አምላክ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፥ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን የሚቃወሙአት ይፈሩ ይጥፉም፥ ጉዳቴንም የሚፈልጉ እፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ። እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ። መዘርዘር ከምችለው በላይ ቢሆንም፥ አፌ ጽድቅህን ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል። በጌታ ኃይል እገባለሁ፥ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ።