መዝሙር 35
35
መዝሙር 35
የተጨቈነ ሰው ጸሎት
የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚታገሉኝን ታገላቸው፤
የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።
2ትልቁንና ትንሹን ጋሻ ያዝ፤
እኔንም ለመርዳት ተነሥ።
3በሚያሳድዱኝ ላይ፣
ጦርና ጭሬ ምዘዝ፤#35፥3 ወይም …መንገድ ዝጋ
ነፍሴንም፣
“የማድንሽ እኔ ነኝ” በላት።
4ሕይወቴን የሚፈልጓት፣
ይቅለሉ፣ ይዋረዱ፤
እኔን ለማጥፋት የሚያሤሩ፣
ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።
5በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ ይሁኑ፤
የእግዚአብሔር መልአክ ያሳድዳቸው።
6መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን፤
የእግዚአብሔር መልአክ ያባርራቸው።
7ያለ ምክንያት ወጥመዳቸውን በስውር አስቀምጠውብኛልና፤
ያለ ምክንያት ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረውላታል።
8ያልታሰበ ጥፋት ይምጣባቸው፤
የሰወሩት ወጥመድ ይያዛቸው፤
ይጠፉም ዘንድ ወደ ጕድጓዱ ይውደቁ።
9ነፍሴም በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤
በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች።
10የሠራ አካላቴ እንዲህ ይልሃል፤
“እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ማን አለ?
ድኻውን ከእርሱ ከሚበረቱ፣
ችግረኛውንና ምስኪኑን ከቀማኞች ታድናለህ።”
11ጨካኝ ምስክሮች ተነሡ፤
ስለማላውቀውም ነገር ጠየቁኝ።
12በበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤
ነፍሴንም ብቸኛ አደረጓት።
13እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤
ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤
ጸሎቴም መልስ ዐጥቶ ወደ ጕያዬ ተመለሰ።
14ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣
እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤
ለእናቴም እንደማለቅስ፣
በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ።
15እነርሱ ግን እኔ ስሰናከል በእልልታ ተሰበሰቡ፤
ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ፤
ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ።
16እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ፤#35፥16 ሰብዓ ሊቃናት እንዲሁ ሲሆን፣ በዕብራይስጥ ግን ምናምንቴ ፌዘኞች ማለት ሊሆን ይችላል።
ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ።
17ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ?
ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፣
ብርቅ ሕይወቴን ከአንበሶች ታደጋት።
18በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤
ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ።
19ከምድር ተነሥተው ጠላቶቼ የሆኑት፣
በላዬ ደስ አይበላቸው፤
እንዲያው የሚጠሉኝ፣
በዐይናቸው አይጣቀሱብኝ።
20የሰላም ንግግር ከአፋቸው አይወጣም፤
ዳሩ ግን በምድሪቱ በጸጥታ በሚኖሩት ላይ፣
ነገር ይሸርባሉ።
21አፋቸውን አስፍተው ከፈቱብኝ፤
“ዕሠይ! ዕሠይ! በዐይናችን አየነው” አሉ።
22 እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አይተሃልና ዝም አትበል፤
ጌታ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ።
23አምላኬ፣ ጌታዬ፤ ለእኔ ለመሟገት ተነሥ!
ልትከራከርልኝም ተንቀሳቀስ።
24 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ በጽድቅህ ፍረድልኝ፤
በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው።
25በልባቸው፣ “ዕሠይ! ያሰብነው ተሳካ!
ዋጥ አደረግነውም” አይበሉ።
26በጭንቀቴ ደስ የሚላቸው፣
ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤
በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣
ዕፍረትንና ውርደትን ይከናነቡ።
27ፍትሕ ማግኘቴን የሚወድዱ፣
እልል ይበሉ፤ ሐሤትም ያድርጉ፤
ዘወትርም፣ “የባሪያው ሰላም ደስ የሚለው፣
እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ።
28አንደበቴ ጽድቅህን፣
ምስጋናህንም ቀኑን ሙሉ ይናገራል።
Currently Selected:
መዝሙር 35: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.