መዝሙር 20:1-7

መዝሙር 20:1-7 NASV

እግዚአብሔር በጭንቅ ቀን ይስማህ፤ የያዕቆብም አምላክ ስም ይጠብቅህ። ከመቅደሱ ረድኤት ይላክልህ፤ ከጽዮንም ደግፎ ይያዝህ። ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ይቀበልልህ። ሴላ የልብህን መሻት ይስጥህ፤ ዕቅድህን ሁሉ ያከናውንልህ። በአንተ ድል ደስ ይበለን፤ በአምላካችን ስም አርማችንን ከፍ እናደርጋለን። እግዚአብሔር የለመንኸውን ሁሉ ይፈጽምልህ። እግዚአብሔር፣ የቀባውን እንደሚያድን አሁን ዐወቅሁ። የማዳን ኀይል ባለው ቀኝ እጁ፣ ከተቀደሰው ሰማይ ይመልስለታል። እነዚህ በሠረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክሕታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው።