መዝሙር 119:73-104

መዝሙር 119:73-104 NASV

እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን። ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ ሥርዐትህን አልረሳሁም። የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው? ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን? በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ። ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ። ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች። ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣ በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ። ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣ በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር። በርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ ሕግህንም ፈልጌአለሁና። ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤ እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ። ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ትእዛዞችህ ምን ጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ። ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ። አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም። ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።