መዝሙር 119:73-104

መዝሙር 119:73-104 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን። ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ ሥርዐትህን አልረሳሁም። የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው? ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን? በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ። ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ። ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች። ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣ በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ። ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣ በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር። በርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ ሕግህንም ፈልጌአለሁና። ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤ እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ። ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ትእዛዞችህ ምን ጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ። ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ። አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም። ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

መዝሙር 119:73-104 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ። በተስፋ ቃልህ ስለምታመን አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው። ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ። በሕግህ ደስ ስለሚለኝ ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ ርኅራኄ አድርግልኝ። በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ ወደ እኔ ይምጡ። ኀፍረት እንዳይደርስብኝ ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ። የአንተን አዳኝነት በሙሉ ልቤ እመኛለሁ። እምነቴን በቃልህ ላይ አድርጌአለሁ። “መቼ ታጽናናኝ ይሆን?” ብዬ የተስፋ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ። ጢስ በሚጤስበት ቤት ተሰቅሎ እንደ ተጨማደደ የወይን ጠጅ አቊማዳ ከጥቅም ውጪ ሆኜአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ሕግህን አልረሳሁም። እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቈይ? የሚያሳድዱኝንስ የምትቀጣቸው መቼ ነው? ሕግህን የማይጠብቁ ትዕቢተኞች እኔን ለማጥመድ ጒድጓድ ቆፍረዋል። ትእዛዞችህ ሁሉ የጸኑ ናቸው፤ ያለ ምክንያት ስለሚያሳድዱኝ እርዳኝ! እነርሱ ሊገድሉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልኩም። ሕግህን እጠብቅ ዘንድ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ ሕይወትን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ቃልህ ዘለዓለማዊ ነው፤ በሰማይም ጸንቶ ይኖራል። ቃልህ በዘመናት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትካት፤ ጸንታም ትኖራለች። ፍጥረቶች ሁሉ አገልጋዮችህ ስለ ሆኑ ትእዛዞችህ እስከ ዛሬ ጸንተው ቈይተዋል። ሕግህ የደስታዬ ምንጭ ባይሆን ኖሮ ከሥቃዬ የተነሣ በሞትኩ ነበር። በሕግህ አማካይነት በሕይወት እንድኖር ጠብቀኸኛልና ሕግህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ስለ ሆንኩ አድነኝ! ትእዛዞችህንም ለማክበር እፈልጋለሁ። ክፉዎች እኔን ለመግደል ያደባሉ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። የሁሉም ነገር ፍጹምነት ወሰን አለው፤ የትእዛዞችህ ፍጹምነት ግን ወሰን የለውም። ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ። ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል። ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ። ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥ ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ። ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥ መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ። ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው! ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል። ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ።

መዝሙር 119:73-104 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ። አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል። እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፥ ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች። ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር። በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ። ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፥ ምስክርህን ግን መረመርሁ። የሥራን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፥ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፥ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፥ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ።