የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 102:1-17

መዝሙር 102:1-17 NASV

እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ። በመከራዬ ቀን ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ መልስልኝ። ዘመኔ እንደ ጢስ ተንኖ ዐልቋልና፤ ዐጥንቶቼም እንደ ማንደጃ ግለዋል። ልቤ ዋግ እንደ መታው ሣር ደርቋል፤ እህል መብላትም ዘንግቻለሁ። ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ፣ ዐጥንቴ ከቈዳዬ ጋራ ተጣበቀ። ይብራ መሰልሁ፤ በፍርስራሽ መካከል እንዳለ ጕጕት ሆንሁ። ያለ እንቅልፍ አድራለሁ፤ በቤቴ ጕልላት ላይ እንዳለ ብቸኛ ወፍ ሆንሁ። ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ ይዘልፉኛል፤ የሚያክፋፉኝም ስሜን እንደ ርግማን ቈጥረውታል። ዐመድ እንደ እህል ቅሜአለሁና፤ መጠጤንም ከእንባ ጋራ ቀላቅያለሁ። ከቍጣህና ከመዓትህ የተነሣ፣ ወደ ላይ አንሥተኸኝ የነበርሁትን መልሰህ ጣልኸኝ። ዘመኖቼ እንደ ምሽት ጥላ ናቸው፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ለዘላለም በዙፋንህ ተቀምጠሃል፤ ስምህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። ትነሣለህ፤ ጽዮንንም በርኅራኄ ዐይን ታያለህ፤ ለርሷ በጎነትህን የምታሳይበት ዘመን ነውና፤ የተወሰነውም ጊዜ ደርሷል። አገልጋዮችህ በድንጋዮቿ ደስ ይሰኛሉ፤ ለዐፈሯም ይሳሳሉ። ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ስም፣ የምድርም ነገሥታት ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ። እግዚአብሔር ጽዮንን መልሶ ይሠራታልና፤ በክብሩም ይገለጣል። እርሱ ወደ ችግረኞች ጸሎት ይመለከታል፤ ልመናቸውንም አይንቅም።