ምሳሌ 5:1-14

ምሳሌ 5:1-14 NASV

ልጄ ሆይ፤ ጥበቤን ልብ በል፤ የማስተዋል ቃሌንም በጥሞና አድምጥ፤ ይህም ልባምነትን ገንዘብ እንድታደርግ፣ ከንፈሮችህም ዕውቀትን እንዲጠብቁ ነው። የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ያንጠባጥባልና፤ አንደበቷም ከቅቤ ይለሰልሳል፤ በመጨረሻ ግን እንደ እሬት ትመርራለች፤ ሁለት አፍ እንዳለውም ስል ሰይፍ ትሆናለች። እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ፤ ርምጃዎቿም በቀጥታ ወደ ሲኦል ያመራሉ። ስለ ሕይወት መንገድ ደንታ የላትም፤ መንገዶቿ ዘወርዋራ ናቸው፤ ለርሷ ግን አይታወቃትም። እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ ከምነግራችሁ ቃል ፈቀቅ አትበሉ። መንገድህን ከርሷ አርቅ፤ በደጃፏም አትለፍ፤ ይኸውም ጕብዝናህን ለሌሎች፣ ዕድሜህንም ለጨካኞች እንዳትሰጥ ነው፤ ባዕዳን በሀብትህ እንዳይፈነጥዙ፣ ልፋትህም የሌላውን ሰው ቤት እንዳያበለጽግ ነው። በዕድሜህ መጨረሻ ታቃሥታለህ፤ ሥጋህና ሰውነትህ ሲከዳህ። እንዲህም ትላለህ፤ “ምነው ተግሣጽን ጠላሁ! ልቤስ ምነው መታረምን ናቀ! የመምህሮቼን ቃል አልሰማሁም፤ አሠልጣኞቼንም አላደመጥኋቸውም፤ በመላው ጉባኤ ፊት፣ ወደ ፍጹም ጥፋት ተቃርቤአለሁ።”