ነህምያ 8:3-6

ነህምያ 8:3-6 NASV

እርሱም በውሃ በር ትይዩ ወደሚገኘው አደባባይ ፊቱን አቅንቶ፣ በወንዶች፣ በሴቶችና በሚያስተውሉ ሰዎች ሁሉ ፊት በመቆም፣ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ፤ ሕዝቡም ሁሉ የሕጉን መጽሐፍ በጥሞና አደመጡ። ጸሓፊው ዕዝራ ለዚሁ ተብሎ በተሠራውና ከፍ ብሎ በሚገኘው የዕንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡም በስተ ቀኙ በኩል መቲትያ፣ ሽማዕ፣ ዓናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ፣ መዕሤያ፣ በስተ ግራው በኩል ደግሞ ፈዳያ፣ ሚሳኤል፣ መልክያ፣ ሐሱም፣ ሐሽበዳና፣ ዘካርያስና ሜሱላም ቆመው ነበር። ዕዝራም መጽሐፉን ከፈተ፤ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ ቆሞ ስለ ነበረ፣ ሁሉም ያዩት ነበረ፣ በከፈተውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ “አሜን! አሜን!” ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።