ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደ ሆነ እይ!” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደ ሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለአካባቢ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዦችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። ይዘው ለፍርድ አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። “ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል። “ ‘የጥፋት ርኩሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በዕርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በእነዚያ ቀናት፣ እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ አሁን ድረስ፣ ከዚህም በኋላ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። “ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ሥጋ ለባሽ ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያ ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው!’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። “በዚያ ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’ “በዚያ ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደ ሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።
ማርቆስ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 13:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች