ማርቆስ 13:1-31

ማርቆስ 13:1-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር ሆይ! እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፤” አለው። በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም “ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው?” ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘እኔ ነኝ፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራብም ትገረፋላችሁ፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸውማል። በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። “ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ፤ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዐይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፤’ ወይም ‘እነሆ፥ ከዚያ አለ፤’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። “በነዚያ ቀኖች ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኀይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል፤ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።

ማርቆስ 13:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደ ሆነ እይ!” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደ ሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለአካባቢ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዦችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። ይዘው ለፍርድ አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። “ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል። “ ‘የጥፋት ርኩሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በዕርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በእነዚያ ቀናት፣ እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ አሁን ድረስ፣ ከዚህም በኋላ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። “ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ሥጋ ለባሽ ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያ ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው!’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። “በዚያ ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’ “በዚያ ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደ ሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።

ማርቆስ 13:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው። በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። በዚያን ጊዜም ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም፦ እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።

ማርቆስ 13:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “መምህር ሆይ! እነዚህን ድንጋዮችና ሕንጻዎች ተመልከት፤ የሚያስደንቁ ናቸው!” ኢየሱስም “እነዚህን ትልልቅ ሕንጻዎች ታያለህን? እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የሚቀር የለም፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና፥ እንድርያስ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “ይህ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ ሁሉ ሊፈጸም ሲቃረብ ምልክቱ ምንድን ነው? እስቲ ንገረን” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ፤ በአቅራቢያችሁ ጦርነት ሲደረግና በሩቅም የጦርነትን ወሬ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ ሁሉ ሊሆን ግድ ነው፤ ይሁን እንጂ መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ጦርነት ያነሣል፤ በየስፍራው የምድር መናወጥና ራብ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ነው። “እናንተም ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በየምኲራቡም ይገርፉአችኋል፤ ምስክር እንድትሆኑኝ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ለፍርድ ትቆማላችሁ። ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ወንጌል ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳረስ ይገባዋል። ሰዎች ይዘው ወደ ፍርድ ሲያቀርቡአችሁ፥ ‘ምን እንናገር ይሆን?’ በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም። ስለዚህ በዚያን ሰዓት የሚሰጣችሁን ብቻ ተናገሩ። ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም። ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። “ደግሞ መገኘት በማይገባው ስፍራ የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር ታያላችሁ፤ ይህንንም አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ምድር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። በቤት ጣራ ላይ ያለ ወደ ቤቱ ወርዶ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ ጊዜ አያጥፋ፤ በእርሻም ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ጊዜ ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! ይህ ሁሉ በክረምት ጊዜ እንዳይሆን ጸልዩ። በዚያን ወራት እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ መከራ ይሆናል፤ ወደ ፊትም እሱን የሚመስል ጭንቀት ከቶ አይደርስም። ጌታ እነዚያን ቀኖች ባያሳጥርማ ኖሮ ማንም መዳን ባልቻለም ነበር፤ ነገር ግን ለተመረጡት ሰዎች ሲባል እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። “እንግዲህ ማንም ቢሆን ‘መሲሕ ይኸው እዚህ ነው!’ ወይም ‘ያው እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይመጣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳሳት ተአምራትና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋሉ። ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁና እንግዲህ ተጠንቀቁ! “በዚያን ጊዜ፥ ከዚያ ሁሉ መከራ በኋላ፥ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማይ ያሉ ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚያም በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ይታያል፤ መላእክቱንም ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም አቅጣጫ ሄደው ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የሚገኙትን፥ ለእርሱ የተመረጡትን ሰዎች ይሰበስባሉ። “የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እንዲሁም እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ከማለፉ በፊት ይህ ሁሉ ይፈጸማል። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ጸንቶ ይኖራል።

ማርቆስ 13:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከቤተ መቅደስ ሲመጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፥ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደሆነ እይ” አለው። ኢየሱስም መልሶ፥ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፥ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድነው?” ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፥ “እኔ እርሱ ነኝ” እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራብ ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። ተይዛችሁ ለፍርድ በምትቀርቡበት ጊዜ፥ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል። የጥፋት ርኩሰት ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በእርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፥ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና። ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያን ጊዜ ማንም፥ “እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?” ቢላችሁ ወይም፥ “እነሆ፤ እዚያ ነው” ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፥ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፥ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። በዚያን ጊዜ፥ ከመከራው በኋላ ፀሓይ ትጨልማለች፥ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኋይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፥ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፥ ቅጠሏ ሲያቆጠቁጥ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፥ በደጅም እንደሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።