የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 13

13
ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስና ስለ ዓለም መጨረሻ እንደተናገረ
(ማቴ. 24፥1-14ሉቃ. 21፥5-19)
1እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር ሆይ! እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ፤” አለው። 2ኢየሱስም መልሶ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፤” አለው።
3በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም 4“ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው?” ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። 5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 6ብዙዎች ‘እኔ ነኝ፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። 7ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። 8ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
9“እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራብም ትገረፋላችሁ፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 10አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። 11ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 12ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸውማል። 13በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
14“ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ 15በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ፤ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፤ 16በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 17በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 18ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 19በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዐይነት ይሆናልና። 20ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። 21በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፤’ ወይም ‘እነሆ፥ ከዚያ አለ፤’ ቢላችሁ አትመኑ፤ 22ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። 23እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ።
ስለ ሰው ልጅ መምጣት
(ማቴ. 24፥29-31ሉቃ. 21፥25-28)
24“በነዚያ ቀኖች ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ 25ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኀይላት ይናወጣሉ። 26በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 27በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል፤ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።
የበለሷ ዛፍ ምሳሌ
(ማቴ. 24፥34-35ሉቃ. 21፥29-33)
28“ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። 29እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። 30እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 31ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።
ኢየሱስ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማንም አያውቅም
(ማቴ. 24፥36-44)
32“ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። 33ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። 34ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፤ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። 35እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና 36ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። 37ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 13