የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 9:51-62

ሉቃስ 9:51-62 NASV

ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፣ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጐጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው። ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ። ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።