ሉቃስ 5:33-39

ሉቃስ 5:33-39 NASV

እነርሱም፣ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አብዛኛውን ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተዎቹ ግን ይበላሉ፤ ይጠጣሉ” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ዐብሯቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዲጾሙ ማድረግ ይቻላልን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በእነዚያም ጊዜያት ይጾማሉ።” ደግሞም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ከአዲስ ልብስ ላይ ቍራጭ ጨርቅ ቀድዶ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢደረግ አዲሱ ልብስ ይቦጨቃል፤ አዲሱም ዕራፊ ለአሮጌው ልብስ አይስማማውም። አዲስ የወይን ጠጅም በአሮጌ አቍማዳ ጨምሮ የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢያደርግ አዲሱ የወይን ጠጅ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ መጨመር አለበት፤ እንግዲህ፣ አሮጌ የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ፣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ ምክንያቱም፣ ‘አሮጌው የተሻለ ነው’ ስለሚል ነው።”