የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 5

5
የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ተጠሩ
5፥1-11 ተጓ ምብ – ማቴ 4፥18-22ማር 1፥16-20ዮሐ 1፥40-42
1ሕዝቡ ዙሪያውን እያጨናነቁት የሚያስተምረውን የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙ፣ ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ሐይቅ#5፥1 የገሊላ ባሕር ነው አጠገብ ቆሞ ነበር፤ 2በዚህ ጊዜ ሁለት ጀልባዎች በሐይቁ ዳርቻ ቆመው አየ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ከጀልባዎቹ ወርደው መረባቸውን ያጥቡ ነበር። 3ከጀልባዎቹም መካከል የስምዖን ወደ ነበረችው ገብቶ፣ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር።
4ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ስምዖንን፣ “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አለው።
5ስምዖንም መልሶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም ዐድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልህ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።
6እንደዚያም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረባቸውም ይበጣጠስ ጀመር። 7በሌላ ጀልባ የነበሩት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲያግዟቸውም በምልክት ጠሯቸው፤ እነርሱም መጥተው ሁለቱን ጀልባዎች በዓሣ ሞሏቸው፣ ጀልባዎቹም መስመጥ ጀመሩ።
8ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው። 9ይህን ያለው እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በያዙት ዓሣ ብዛት ስለ ተደነቁ ነው፤ 10ደግሞም የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች፣ ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ።
ኢየሱስም ስምዖንን፣ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው። 11እነርሱም ጀልባዎቹን ወደ ምድር ካስጠጉ በኋላ፣ ሁሉን ትተው ተከተሉት።
ለምጻሙ ሰው
5፥12-14 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥2-4ማር 1፥40-44
12ኢየሱስ ከከተሞች በአንዱ በነበረበት ጊዜ፣ አንድ ለምጽ የወረሰው#5፥12 የግሪኩ ቃል የግድ ከለምጽ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችንም ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል። ሰው በዚያው ከተማ ነበር፤ ይህ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በፊቱ ተደፋና፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው።
13ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ጠፋለት።
14ኢየሱስም፣ “ይህን ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱ ምስክር እንዲሆንም ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” ሲል አዘዘው።
15ይሁን እንጂ ስለ እርሱ የሚወራው ወሬ ይበልጥ እየሰፋ ሄደ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችም እርሱ የሚናገረውን ለመስማትና ካለባቸው ደዌ ለመፈወስ ይሰበሰቡ ነበር። 16ኢየሱስ ግን ብዙ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወጥቶ ይጸልይ ነበር።
ኢየሱስ ሽባውን ሰው ፈወሰ
5፥18-26 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥2-8ማር 2፥3-12
17አንድ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ነበር፤ በዚያም ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ተቀምጠው ነበር፤ ይፈውስም ዘንድ የጌታ ኀይል ከእርሱ ጋር ነበረ። 18በዚያን ጊዜም፣ ሰዎች አንድ ሽባ በዐልጋ ተሸክመው አመጡ፤ ኢየሱስ ፊት ለማኖርም ወደ ቤት ሊያስገቡት ሞከሩ፤ 19ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ቤቱ ውስጥ ማስገባት ስላቃታቸው፣ ጣራው ላይ ወጥተው የቤቱን ክዳን በመንደል በሽተኛውን ከነዐልጋው በሕዝቡ መካከል ቀጥታ ኢየሱስ ፊት አወረዱት።
20ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ “አንተ ሰው፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።
21ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም፣ “ይህ አምላክን በመዳፈር እንዲህ የሚናገር ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ኀጢአትን ሊያስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር።
22ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስለ ተረዳ እንዲህ አላቸው፤ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ? 23‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል? 24ነገር ግን ይህን ያልሁት የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ ነው።” ከዚያም ሽባውን ሰው፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው። 25እርሱም ወዲያው ተነሥቶ በፊታቸው ቆመ፤ ተኝቶበት የነበረውንም ተሸክሞ፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። 26በዚህ ጊዜ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ “ዛሬ እኮ ድንቅ ነገር አየን” እያሉ በፍርሀት ተዋጡ።
የሌዊ መጠራት
5፥27-32 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥9-13ማር 2፥14-17
27ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ ሌዊ የተባለ አንድ ቀረጥ ሰብሳቢም በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ 28እርሱም ሁሉን ትቶ ተነሥቶ ተከተለው።
29ሌዊም ለኢየሱስ በቤቱ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ነበር። 30ፈሪሳውያንና ጸሐፍታቸውም “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ‘ከኀጢአተኞች’ ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” እያሉ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጕረመረሙ።
31ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ 32እኔም ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልመልስ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”
ኢየሱስ ስለ ጾም ተጠየቀ
5፥33-39 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥14-17ማር 2፥18-22
33እነርሱም፣ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አብዛኛውን ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተዎቹ ግን ዘወትር ይበላሉ፤ ይጠጣሉ” አሉት።
34ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው አብሯቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዲጾሙ ማድረግ ይቻላልን? 35ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።”
36ደግሞም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ከአዲስ ልብስ ላይ ዕራፊ ቀድዶ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢያደርግ አዲሱን ልብስ ይቀድደዋል፤ አዲሱም እራፊ ለአሮጌው ልብስ አይስማማውም። 37አዲስ የወይን ጠጅም በአሮጌ አቍማዳ ጨምሮ የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢያደርግ አዲሱ የወይን ጠጅ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። 38ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ መጨመር አለበት፤ 39እንግዲህ፣ አሮጌ የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ፣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ ምክንያቱም፣ ‘አሮጌው የተሻለ ነው’ ስለሚል ነው።”

Currently Selected:

ሉቃስ 5: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ