ሉቃስ 5:17-39

ሉቃስ 5:17-39 NASV

አንድ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ነበር፤ በዚያም ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ተቀምጠው ነበር፤ ይፈውስም ዘንድ የጌታ ኀይል ከርሱ ጋራ ነበረ። በዚያ ጊዜም፣ ሰዎች አንድ ሽባ በቃሬዛ ተሸክመው አመጡ፤ ኢየሱስ ፊት ለማኖርም ወደ ቤት ሊያስገቡት ሞከሩ፤ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ቤቱ ውስጥ ማስገባት ስላቃታቸው፣ ጣራው ላይ ወጥተው የቤቱን ክዳን በመንደል በሽተኛውን ከነዐልጋው በሕዝቡ መካከል ቀጥታ ኢየሱስ ፊት አወረዱት። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ “አንተ ሰው፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም፣ “አምላክን በመሳደብ እንዲህ የሚናገር ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስለ ተረዳ እንዲህ አላቸው፤ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ? ‘ኀጢአትህ ተሰረየልህ’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀልላል? ነገር ግን ይህን ያልሁት የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ ነው።” ከዚያም ሽባውን ሰው፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው። እርሱም ወዲያው ተነሥቶ በፊታቸው ቆመ፤ ተኝቶበት የነበረውንም ተሸክሞ፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። በዚህ ጊዜ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ “ዛሬ እኮ ድንቅ ነገር አየን” እያሉ በፍርሀት ተዋጡ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ ሌዊ የተባለ አንድ ቀረጥ ሰብሳቢም በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ሁሉን ትቶ ተነሥቶ ተከተለው። ሌዊም ለኢየሱስ በቤቱ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋራ በማእድ ተቀምጠው ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍታቸውም “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ‘ከኀጢአተኞች’ ጋራ የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” እያሉ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጕረመረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ እኔም ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልመልስ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።” እነርሱም፣ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አብዛኛውን ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተዎቹ ግን ይበላሉ፤ ይጠጣሉ” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ዐብሯቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዲጾሙ ማድረግ ይቻላልን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በእነዚያም ጊዜያት ይጾማሉ።” ደግሞም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ከአዲስ ልብስ ላይ ቍራጭ ጨርቅ ቀድዶ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢደረግ አዲሱ ልብስ ይቦጨቃል፤ አዲሱም ዕራፊ ለአሮጌው ልብስ አይስማማውም። አዲስ የወይን ጠጅም በአሮጌ አቍማዳ ጨምሮ የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢያደርግ አዲሱ የወይን ጠጅ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ መጨመር አለበት፤ እንግዲህ፣ አሮጌ የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ፣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ ምክንያቱም፣ ‘አሮጌው የተሻለ ነው’ ስለሚል ነው።”