ሉቃስ 22:63-71

ሉቃስ 22:63-71 NASV

ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው፣ “ትንቢት ተናገር! ማነው የመታህ?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር። በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጓቸው ፊት አቀረቡት። እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስኪ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ብጠይቃችሁም አትመልሱም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው። እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።