ሉቃስ 22:63-71
ሉቃስ 22:63-71 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስን ይዘውት የነበሩት ሰዎችም ይዘባበቱበትና ይደበድቡት ነበር። ሸፍነውም ፊቱን በጥፊ ይመቱት ነበር፤ “ፊትህን በጥፊ የመታህ ማነው? ንገረን” እያሉም ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት። “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፤ እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም። ብጠይቃችሁም አትመልሱልኝም፤ ወይም አትተዉኝም። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” ሁሉም፥ “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት፤ እርሱም፥ “እኔ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ” አላቸው። እነርሱም፥ “ስለ እርሱ ምን ምስክር እንሻለን? እኛ ራሳችን ሲናገር ሰምተናል” አሉ።
ሉቃስ 22:63-71 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው፣ “ትንቢት ተናገር! ማነው የመታህ?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር። በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጓቸው ፊት አቀረቡት። እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስኪ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ብጠይቃችሁም አትመልሱም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው። እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።
ሉቃስ 22:63-71 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና፦ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። ሁላቸውም፦ እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም፦ እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። እነርሱም፦ ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።
ሉቃስ 22:63-71 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ይዘውት የነበሩ ሰዎች በእርሱ ላይ ያፌዙበትና ይደበድቡትም ነበር። ፊቱንም እየሸፈኑ፥ “ማን ነው የመታህ? ነቢይ ከሆንክ እስቲ ዕወቅ!” ይሉት ነበር። በእርሱም ላይ ብዙ ነገር እየተናገሩ ይሰድቡት ነበር። በነጋ ጊዜም የሕዝብ ሽማግሌዎች፥ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም ወደ ሸንጎአቸው አመጡት። እንዲህም አሉት፦ “እስቲ አንተ መሲሕ ከሆንክ ንገረን፤” እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ጥያቄም ባቀርብላችሁ አትመልሱልኝም፤ ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ይቀመጣል።” ሁሉም በአንድነት “ታዲያ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አዎ፥ እናንተ እንዳላችሁት ነው” አላቸው። እነርሱም “እንግዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? እነሆ፥ ከአፉ የወጣውን ቃል እኛ ራሳችን ሰምተናል!” አሉ።
ሉቃስ 22:63-71 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይቀልዱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ፊቱንም እየሸፈኑ “በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር፤” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። ሲነጋም የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና “አንተ መሢሕ ነህን? እስቲ ንገረን፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም፤ አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል።” ሁላቸውም “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም “እኔ እንደሆንሁ እናንተ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። እነርሱም “ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል?” አሉ።