ሉቃስ 21:1-19

ሉቃስ 21:1-19 NASV

ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በቤተ መቅደሱ መባ መሰብሰቢያ ውስጥ መባቸውን ሲጨምሩ አየ። ደግሞም አንዲት ድኻ መበለት ሁለት ትንንሽ የናስ ሳንቲሞች በዚያ ስትጨምር ተመለከተ። እንዲህም አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉም የበለጠ ጨመረች። እነዚህ ሰዎች የሰጡት ከትርፋቸው ላይ ሲሆን፣ እርሷ ግን የሰጠችው ከጕድለቷ ያላትን መተዳደሪያዋን በሙሉ ነው።” ከደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ በውብ ድንጋዮችና በስእለት ስጦታዎች እንዳማረ ሲነጋገሩ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ይህ የምታዩት ሁሉ ሳይፈርስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደ ተካበ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል።” እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? ደግሞም ይህ እንደሚሆን ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ በማለት፣ ደግሞም፣ ‘ጊዜው ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እናንተ ግን እነርሱን አትከተሏቸው። ስለ ጦርነትና ስለ ሕዝብ ዐመፅ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ መሆን የሚገባው ነውና፤ መጨረሻው ግን ወዲያውኑ አይሆንም።” ቀጥሎም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ አስፈሪ ነገር እንዲሁም ከሰማይ ታላቅ ምልክት ይሆናል። “ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ሰዎች ያስሯችኋል፤ ያሳድዷችኋል፤ ወደ ምኵራቦችና ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧችኋል፤ በነገሥታትና በገዦች ፊት ለፍርድ ያቀርቧችኋል፤ ይህም ሁሉ በስሜ ምክንያት ይደርስባችኋል። ይህም ለመመስከር ጥሩ ዕድል ይሆንላችኋል። ስለዚህ ምን መልስ እንሰጣለን በማለት አስቀድማችሁ እንዳትጨነቁ ይህን ልብ በሉ፤ ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ ሊቋቋሙትና ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ቃልና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጕር አንዷ እንኳ አትጠፋም፤ ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።