ሉቃስ 14:26-33

ሉቃስ 14:26-33 NASV

“ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱንና እናቱን ሚስቱንና ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፣ የራሱንም ሕይወት እንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፤ የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። “ከእናንተ አንድ ሰው ሕንጻ ለመሥራት ቢፈልግ፣ መደምደም መቻል አለመቻሉን በመጀመሪያ ተቀምጦ ዋጋውን የማይተምን ማነው? መሠረቱን ጥሎ መደምደም ቢያቅተው፣ ያዩት ሁሉ ይዘባበቱበታል፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ይህ ሰው ማነጽ ጀምሮ ነበር፤ መደምደም ግን አቃተው።’ “ወይም አንድ ንጉሥ ከሌላው ንጉሥ ጋራ ጦርነት ሊገጥም በሚነሣበት ጊዜ፣ ሃያ ሺሕ ሰራዊት አስከትቶ የሚመጣበትን ንጉሥ፣ በዐሥር ሺሕ ሰራዊት መመከት እንደሚችል ተቀምጦ የማይመክር ማን ነው? መቋቋም የማይችል ከሆነ፣ ሌላው ንጉሥ ገና ሩቅ ሳለ፣ መልእክተኞች ልኮ ዕርቅ ይጠይቃል። እንደዚሁም፣ ከእናንተ ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።