ሉቃስ 1:26-33

ሉቃስ 1:26-33 NASV

በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋራ ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”