ዘሌዋውያን 9
9
ካህናቱ አገልግሎታቸውን ጀመሩ
1በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንንና ልጆቹን እንዲሁም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራቸው። 2አሮንንም እንዲህ አለው፤ “የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ እንቦሳ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ አውራ በግ ወስደህ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርባቸው፤ ሁለቱም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ። 3እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፤ ‘ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት እንከን የሌለባቸውን የአንድ ዓመት እንቦሳና የአንድ ዓመት ጠቦት፣ 4ለኅብረት መሥዋዕት#9፥4 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል፤ እንዲሁም 18፥22 ይመ። አንድ በሬና#9፥4 የዕብራይስጥ ቃል ተባዕትና እንስትን ሊያጠቃልል ይችላል፤ እንዲሁም 18፡19 ይመ አንድ አውራ በግ በዘይት ከተለወሰ የእህል ቍርባን ጋር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመሠዋት አቅርቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ይገለጥላችኋልና።’ ”
5እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሙ። 6ሙሴም፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ፣ እንድታደርጉት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዛችሁ ይህ ነው” አለ።
7ሙሴ አሮንን፣ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተስርይላቸውም” አለው።
8አሮንም ወደ መሠዊያው መጥቶ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት የቀረበውን እንቦሳ ዐረደው። 9ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ግርጌ አፈሰሰው። 10እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት የኀጢአት መሥዋዕቱን ሥብ፣ ኵላሊቶቹንና የጕበቱን ሽፋን በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ 11ሥጋውንና ቍርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።
12ከዚህ በኋላ አሮን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዐረደ፤ ልጆቹ ደሙን አቀበሉት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 13ልጆቹም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ብልት አንድ በአንድ፣ ጭንቅላቱን ሳይቀር አምጥተው ሰጡት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ዐጥቦ በመሠዊያው ላይ ካለው ከሚቃጠለው መሥዋዕት በላይ አቃጠለ። 15አሮንም የሕዝቡን መሥዋዕት አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ ዐረደው፤ እንደ ፊተኛው ሁሉ ይህንም በኀጢአት መሥዋዕትነት ሠዋው።
16የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አምጥቶ በሥርዐቱ መሠረት አቀረበው። 17የእህል ቍርባኑን አመጣ፤ ከላዩም ዕፍኝ ሙሉ ወስዶ ጧት ጧት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ።
18አሮንም ስለ ሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት የቀረቡትን በሬውንና አውራ በጉን ዐረደ፤ ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 19የበሬውንና የአውራ በጉን ሥብ፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፤ ኵላሊቶቹንና የጕበቱን ሽፋን፣ 20በፍርምባዎቹ ላይ አስቀመጡ፤ አሮንም ሥቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21ፍርምባዎቹንና የቀኝ ወርቹንም ሙሴ ባዘዘው መሠረት፣ የመወዝወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዘው።
22አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘርግቶ ባረካቸው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱን፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ወረደ።
23ከዚህ በኋላ፣ ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ከዚያ ሲወጡም ሕዝቡን ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24እሳት ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ፣ በመሠዊያው ላይ የነበረውን በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ባዩ ጊዜ እልል አሉ፤ በግንባራቸውም ተደፉ።
Currently Selected:
ዘሌዋውያን 9: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.