የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘሌዋውያን 10

10
የናዳብና የአብዩድ መሞት
1የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ። 2ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ሞቱ። 3ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ)
“ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣
ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤
በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣
እከበራለሁ’
ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ።
4ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው። 5እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።
6ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ ጠጕራችሁን አትንጩ፤#10፥6 ወይም አትላጩ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ። 7የእግዚአብሔር (ያህዌ) የመቅቢያ ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን አትውጡ።” እነርሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።
8 እግዚአብሔርም (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ 9“እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው። 10የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኩሱንና ንጹሑን ለዩ፤ 11እግዚአብሔርም (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።”
12ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የእህል ቍርባን የቀረውን ወስዳችሁ ያለ እርሾ ጋግሩት፤ እጅግ ቅዱስ ስለሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት። 13ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት ያንተና የልጆችህ ድርሻ ይህ ስለሆነ፣ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት፤ እንዲህ ታዝዣለሁና። 14ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት#10፥14 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል ላይ የእናንተ ድርሻ ሆኖ ስለ ተሰጠ፣ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ብሉት። 15የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋር ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”
16ሙሴ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበውን ፍየል አጥብቆ ፈለገ፤ መቃጠሉንም በተረዳ ጊዜ የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ 17“የኀጢአት መሥዋዕቱን ለምን በተቀደሰው ስፍራ አልበላችሁትም? እጅግ የተቀደሰ ነው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ስርየት በማስገኘት የሕዝቡን ኀጢአት እንድታስወግዱበት የተሰጣችሁ ነበር፤ 18ደሙ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ስላልገባ፣ በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት ፍየሉን በተቀደሰው ስፍራ መብላት ይገባችሁ ነበር።”
19አሮንም ሙሴን፣ “እነሆ፤ በዛሬው ቀን የኀጢአት መሥዋዕታቸውንና የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ፤ እኔም እንዲህ ያለ ነገር የደረሰብኝ ሰው ነኝ፤ ታዲያ፣ ዛሬ የኀጢአት መሥዋዕቱን ብበላ ኖሮ እግዚአብሔርስ (ያህዌ) ደስ ይለው ኖሯልን?” አለው። 20ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 10: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ