የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘሌዋውያን 4:27-35

ዘሌዋውያን 4:27-35 NASV

“ ‘ከሕዝቡ መካከል አንዱ ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው። ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ፍየል ስለ ፈጸመው ኀጢአት የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። እጁን ለኀጢአት መሥዋዕት በቀረበችው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም ይረዳት። ካህኑ በጣቱ ከደሟ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። ሥቡን ከኅብረት መሥዋዕት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። “ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የበግ ጠቦት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ያቅርብ። እጁን በጠቦቷ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረዳት። ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። ሥቡ ከኅብረት መሥዋዕት ጠቦት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በእሳት በሚቀርበው መሥዋዕት ላይ ያቃጥለው። በዚህ መሠረት ሰውየው የሠራውን ኀጢአት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።