ዘሌዋውያን 26:40-46

ዘሌዋውያን 26:40-46 NASV

“ ‘ነገር ግን ለእኔ ያልታመኑበትንና በእኔም ላይ ያመፁበትን የራሳቸውን ኀጢአትና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ይኸውም፣ እኔ ጠላት እንድሆንባቸውና ወደ ጠላቶቻቸው ምድር እንድሰድዳቸው ያደረገኝን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድና ስለ ኀጢአታቸው የሚገባውን ቅጣት ቢቀበሉ፣ በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይሥሐቅም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ ምድሪቱንም ዐስባታለሁ። ምድሪቱ እነርሱ ለቅቀዋት ስለ ሄዱ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱ በሌሉበት ጊዜም ባድማ ሆና በሰንበቷ ትደሰታለች፤ ሕጌን በማቃለላቸውና ሥርዐቴን በመናቃቸው፣ የኀጢአታቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። በዚህ ሁሉ ግን ከእነርሱ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን በማፍረስ፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ፈጽሜ እስካጠፋቸው ድረስ አልተዋቸውም፤ አልጸየፋቸውምም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። ስለ እነርሱም ስል፣ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው ጋራ የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” እግዚአብሔር በራሱና በእስራኤላውያን መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ በኩል ያቆማቸው ሥርዐቶች፣ ሕጎችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።