በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋራ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋራ ነበረ። ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። ሰዎች ሁሉ በርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው። አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር። ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ በግልጽ መሰከረ። እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ። በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ። ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ እኔ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የማይገባኝ እርሱ ነው።” ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።” ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።”
ዮሐንስ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 1:1-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos