የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 1:1-34

ዮሐንስ 1:1-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በመ​ጀ​መ​ሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነበረ። ይህም በመ​ጀ​መ​ሪያ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉም በእ​ርሱ ሆነ፤ ከሆ​ነ​ውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ሕይ​ወት በእ​ርሱ ነበረ፥ ሕይ​ወ​ትም የሰው ብር​ሃን ነበረ፤ ብር​ሃ​ንም በጨ​ለማ ያበ​ራል፤ ጨለ​ማም አላ​ገ​ኘ​ውም። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የተ​ላከ ስሙ ዮሐ​ንስ የሚ​ባል አንድ ሰው ነበር። እር​ሱም ሁሉ በእ​ርሱ በኩል እን​ዲ​ያ​ምን ስለ ብር​ሃን ይመ​ሰ​ክር ዘንድ ለም​ስ​ክ​ር​ነት መጣ። ስለ ብር​ሃን ምስ​ክር ሊሆን መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብር​ሃን አል​ነ​በ​ረም። ለሰው ሁሉ የሚ​ያ​በ​ራው እው​ነ​ተ​ኛው ብር​ሃ​ንስ ወደ ዓለም የመ​ጣው ነው። በዓ​ለም ነበረ፤ ዓለ​ሙም በእ​ርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላ​ወ​ቀ​ውም። ወደ ወገ​ኖቹ መጣ፤ ወገ​ኖቹ ግን አል​ተ​ቀ​በ​ሉ​ትም። ለተ​ቀ​በ​ሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚ​ያ​ምኑ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች እን​ዲ​ሆኑ ሥል​ጣ​ንን ሰጣ​ቸው። እነ​ር​ሱም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተወ​ለዱ እንጂ ከሥ​ጋ​ዊና ከደ​ማዊ ግብር ወይም ከወ​ን​ድና ከሴት ፈቃድ አል​ተ​ወ​ለ​ዱም። ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእ​ኛም አደረ፤ ለአ​ባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብ​ሩን አየን፤ ጸጋ​ንና እው​ነ​ትን የተ​መላ ነው። ምስ​ክሩ ዮሐ​ንስ ስለ እርሱ ድም​ፁን ከፍ አድ​ርጎ ተና​ገረ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “እኔ ስለ እርሱ ከእኔ በፊት የነ​በረ ከእኔ በኋላ ይመ​ጣል ያል​ኋ​ችሁ ሰው ይህ ነው፥ እርሱ ከእኔ አስ​ቀ​ድሞ ነበ​ረና።” እኛም ሁላ​ችን ከሙ​ላቱ በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀ​በ​ልን። ኦሪት በሙሴ ተሰ​ጥ​ታን ነበ​ርና፤ ጸጋና እው​ነት ግን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ሆነ​ልን። በአ​ባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ገለ​ጠ​ልን እንጂ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንስ ከቶ ያየው የለም። አይ​ሁድ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ይጠ​ይ​ቁት ዘንድ ካህ​ና​ት​ንና ሌዋ​ው​ያ​ንን ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም በላኩ ጊዜ የዮ​ሐ​ንስ ምስ​ክ​ር​ነት ይህ ነው። እር​ሱም፥ “እኔ ክር​ስ​ቶስ አይ​ደ​ለ​ሁም” ብሎ አመነ እንጂ አል​ካ​ደም። “እን​ኪያ አንተ ማነህ? አንተ ኤል​ያስ ነህን?” ብለው ጠየ​ቁት፤ “አይ​ደ​ለ​ሁም” አለ፤ “እን​ኪያ አንተ ነቢዩ ነህን?” አሉት፤ “አይ​ደ​ለ​ሁም” አለ። “እን​ኪ​ያስ አንተ ማነህ? ለላ​ኩ​ንም መልስ እን​ድ​ን​ሰጥ ስለ ራስህ ማን ትላ​ለህ?” አሉት። እር​ሱም፥ “ነቢዩ ኢሳ​ይ​ያስ እንደ ተና​ገረ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ገድ ጥረጉ እያለ በም​ድረ በዳ የሚ​ሰ​ብክ የዐ​ዋጅ ነጋሪ ድምፅ እኔ ነኝ” አለ። የተ​ላ​ኩ​ትም ከፈ​ሪ​ሳ​ው​ያን ነበሩ። “እን​ኪ​ያስ ክር​ስ​ቶ​ስን ካል​ሆ​ንህ፥ ኤል​ያ​ስ​ንም ካል​ሆ​ንህ፥ ነቢ​ይ​ንም ካል​ሆ​ንህ ለምን ታጠ​ም​ቃ​ለህ?” ብለው ጠየ​ቁት። ዮሐ​ን​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እኔ በውኃ አጠ​ም​ቃ​ች​ኋ​ለሁ፤ ነገር ግን እና​ንተ የማ​ታ​ው​ቁት በመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ ቆሞ​አል። ከእኔ በኋላ የሚ​መ​ጣው፥ ከእኔ በፊት የነ​በ​ረው፥ የጫ​ማ​ውን ጠፍር ልፈታ እንኳ የማ​ይ​ገ​ባኝ ነው።” ዮሐ​ንስ ያጠ​ም​ቅ​በት በነ​በ​ረው በዮ​ር​ዳ​ኖስ ማዶ በቢ​ታ​ንያ በቤተ ራባ እን​ዲህ ሆነ። በማ​ግ​ሥ​ቱም ዮሐ​ንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን አይቶ እን​ዲህ አለ፤ “እነሆ፥ የዓ​ለ​ሙን ኀጢ​ኣት የሚ​ያ​ስ​ወ​ግድ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በግ። ከእኔ በፊት የነ​በረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመ​ጣል ብዬ ስለ እርሱ የነ​ገ​ር​ኋ​ችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስ​ቀ​ድሞ ነበ​ርና። እኔ አላ​ው​ቀ​ውም ነበር፤ ነገር ግን እስ​ራ​ኤል እን​ዲ​ያ​ው​ቁት ስለ​ዚህ እኔ በውኃ ላጠ​ምቅ መጣሁ።” ዮሐ​ን​ስም ምስ​ክ​ር​ነ​ቱን እን​ዲህ ብሎ ተና​ገረ፥ “መን​ፈስ ቅዱስ ከሰ​ማይ እንደ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀ​መጥ አየሁ። እኔም አላ​ው​ቀ​ውም ነበር፤ ነገር ግን በውኃ እን​ዳ​ጠ​ምቅ የላ​ከኝ እርሱ መን​ፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀ​መ​ጥ​በት የም​ታ​የው በመ​ን​ፈስ ቅዱስ የሚ​ያ​ጠ​ምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም ራሴ አይ​ቻ​ለሁ፤ እር​ሱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ እንደ ሆነ እኔ ምስ​ክሩ ነኝ።”

ዮሐንስ 1:1-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋራ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋራ ነበረ። ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። ሰዎች ሁሉ በርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው። አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር። ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ በግልጽ መሰከረ። እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ። በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ። ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ እኔ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የማይገባኝ እርሱ ነው።” ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።” ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።”

ዮሐንስ 1:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም አልካደምም እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ። እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት። እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።

ዮሐንስ 1:1-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጠረ፤ ከተፈጠረው ሁሉ፥ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ ይህም ሕይወት የሰዎች ብርሃን ነበረ። ብርሃን በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንን አያሸንፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ መጣ። እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱም በዓለም ነበረ፤ ዓለምም የተፈጠረው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ይሁን እንጂ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሰው ዘር፥ ማለትም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በመካከላችን ኖረ፤ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ እንዳለው ያለውን ክብሩን አይተናል። ዮሐንስም “ ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ብዬ የነገርኳችሁ እነሆ፥ ይህ ነው” እያለ መሰከረ። ከእርሱ የጸጋ ሙላት እኛ ሁላችን በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጠ፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድያ ልጁ ብቻ ገለጠው። የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ወደ ዮሐንስ ልከው፦ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ባስጠየቁት ጊዜ የሰጠው ምስክርነት የሚከተለው ነው፤ እርሱ “እኔ መሲሕ አይደለሁም” ሲል መሰከረ እንጂ አልካደም። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አይደለሁም” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም “ይመጣል የተባለው ነቢይ ነህን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” አለ። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልሱን እንድንነግር ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረው እኔ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። ሰዎቹ የተላኩት ከፈሪሳውያን ነበረ፤ ስለዚህ “አንተ መሲሕ ወይም ኤልያስ ወይም ይመጣል የተባለው ነቢይ ካልሆንክ ታዲያ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የማጠምቀው በውሃ ነው፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። እርሱ ከእኔ በኋላ የሚመጣ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም።” ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነው። በማግስቱ ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ይህ ነው! ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ያልኳችሁ ይህ ነው። እኔም ራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲገለጥ እኔ በውሃ እያጠመቅሁ መጣሁ።” ቀጥሎም ዮሐንስ እንዲህ ሲል መሰከረ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ከሰማይ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍበት አየሁ፤ እኔ ራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝ፥ ‘መንፈስ ቅዱስ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው’ ሲል ነግሮኛል። እኔም ይህን አይቼአለሁ፤ ስለዚህ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እመሰክራለሁ።”

ዮሐንስ 1:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የሆነ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰዎች ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤ ሁሉም በእርሱ በኩል ያምኑ ዘንድ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለም ግን አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን ሥልጣን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ “‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤’ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” እኛ ሁላችንም ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠው። አይሁድም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም፤ አልካደምም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ መሰከረ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት። “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህን?” “አይደለሁም” ብሎ መለሰ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ፤ “እንግዲያውስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የተገበሁ አይደለሁም” አላቸው። ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። ‘አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይበልጣል፤’ ብዬ ስለ እርሱ የተናገርሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁት።” ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲኖር አየሁ። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ ‘መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው፤’ አለኝ። እኔም አይቻለሁ፥ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።”

ዮሐንስ 1:1-34

ዮሐንስ 1:1-34 NASV