ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ “በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ በዚያም ይህን መልእክት ዐውጅ፤ “ ‘እግዚአብሔርን ለማምለክ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሕዝብ ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፤ እኔም በዚህ ስፍራ እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። “ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው” እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ። መንገዳችሁንና ሥራችሁን በርግጥ ብታሳምሩ፣ በመካከላችሁ ቅንነት ቢኖር፣ መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈስሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣ ለአባቶቻችሁ ለዘላለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው ምድር፣ በዚህ ስፍራ አኖራችኋለሁ። እናንተ ግን፣ ከንቱ በሆኑ የሐሰት ቃላት ታምናችኋል። “ ‘ትሰርቃላችሁ፤ ሰው ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ በሐሰት ትምላላችሁ፤ ለበኣል ታጥናላችሁ፤ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ትከተላላችሁ፤ ስሜ ወደሚጠራበት ወደዚህ ቤት መጥታችሁ በፊቴ ትቆሙና “ደኅና ነን” እያላችሁ እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ታደርጋላችሁ። ስሜ የሚጠራበት፣ ይህ ቤት በእናንተ ዘንድ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኗልን? እነሆ፤ የምታደርጉትን ነገር አይቻለሁ ይላል እግዚአብሔር።
ኤርምያስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 7:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች