የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤርምያስ 32

32
ኤርምያስ የዕርሻ ቦታ መግዛቱ
1የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፣ ይኸውም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዐሥራ ስምንተኛ ዘመነ መንግሥት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ 2በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተዘግቶበት ነበር።
3የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም እንዲህ በማለት አሳስሮት ነበር፤ “እንዴት እንደዚህ ያለ ትንቢት ትናገራለህ? ‘እግዚአብሔር፤ “ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል። 4የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፎ ይሰጣል፤ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፤ በዐይኖቹም ያየዋል እንጂ ከባቢሎናውያን#32፥4 ወይም ከለዳውያን፤ በ5፡24፡25፡28፡29 እና 43 ይመ። እጅ አያመልጥም። 5ሴዴቅያስንም ወደ ባቢሎን ይወስደዋል፤ በፍርዴ እስከምጐበኘውም ድረስ በዚያ ይቈያል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ከባቢሎናውያን ጋር ብትዋጉ አይሳካላችሁም” ይላል’ ትላለህ።”
6ኤርምያስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ አለ፦ 7“የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፣ ‘የመቤዠት መብት የአንተ ስለሆነ፣ በዓናቶት ያለውን መሬቴን ግዛኝ’ ይልሃል።”
8 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ፣ የአጎቴ ልጅ አናምኤል ወደ ዘብ ጠባቂዎቹ አደባባይ መጥቶ፣ “የመቤዠቱን ርስት የማድረጉ መብት የአንተ ስለሆነ፣ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን መሬቴን ለራስህ እንዲሆን ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ ዐወቅሁ፤ 9ስለዚህ በዓናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል#32፥9 200 ግራም ያህል ነው። ብር መዝኜ ሰጠሁት። 10በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት። 11የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዥውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤ 12በአጎቴም ልጅ በአናምኤልና በውሉ ላይ በፈረሙት ምስክሮች ፊት እንዲሁም በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ሁሉ ፊት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።
13በእነርሱ ፊት ለባሮክ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠሁት፤ 14“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የታሸገውንና ያልታሸገውን፣ ሁለቱን የግዥ ውል ሰነዶች ለብዙ ጊዜ ሳይበላሹ እንዲቈዩ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው። 15የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ሰዎች በዚህ ምድር ቤት፣ የዕርሻ ቦታና የወይን አትክልት ስፍራ እንደ ገና ይገዛሉ።’
16“ለኔርያ ልጅ ለባሮክ የግዥ ውሉን ከሰጠሁ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤
17“አቤት፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም። 18ፍቅርና ቸርነትን ለእልፍ አእላፍ ታሳያለህ፤ ይሁን እንጂ የአባቶችን በደል ከእነርሱ በኋላ በሚነሡ ልጆቻቸው ጕያ ትመልሳለህ፤ ስምህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ፣ ታላቅና ኀያል አምላክ ሆይ፤ 19ዕቅድህ ታላቅ፣ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ዐይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ። 20በግብፅ ታምራትንና ድንቆችን አደረግህ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሰው ልጆች ሁሉ መካከል እንደዚያው እያደረግህ ዛሬም ስምህ ገናና ነው። 21በታምራትና በድንቅ፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ እጅግ በሚያስፈራም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ አወጣህ። 22ለአባቶቻችን ልትሰጣቸው የማልህላቸውን፣ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ይህችን ምድር ሰጠሃቸው፤ 23ወደዚያም ገብተው ወረሷት፤ ነገር ግን አልታዘዙህም፤ ሕግህንም አልጠበቁም፤ እንዲያደርጉት ያዘዝሃቸውን ከቶ አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ሁሉ ጥፋት በላያቸው አመጣህ።
24“እነሆ፤ ከተማዪቱን ለመያዝ የዐፈር ድልድል በዙሪያዋ ተሠርቷል፤ ከሰይፍ፣ ከራብና ከቸነፈር የተነሣ ከተማዪቱን ለሚወጓት ለባቢሎናውያን ዐልፋ ልትሰጥ ነው፤ እንደምታየውም የተናገርኸው እየተፈጸመ ነው። 25አንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተማዪቱ ለባቢሎናውያን ዐልፋ እየተሰጠች፣ ‘መሬቱን በብር ግዛ፤ ግዥውንም በምስክሮች ፊት ፈጽም’ ትለኛለህ።”
26ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 27“እነሆ፤ እኔ የሰው ልጆች ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ የሚያቅተኝ ነገር አለን? 28ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እነሆ፤ ይህችን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል። 29ከተማዪቱን የሚወጓት ባቢሎናውያን ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቡ በየሰገነቱ ላይ ለበኣል ያጠኑባቸውንና ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀረቡባቸውን ቤቶች ጭምር ያነድዳሉ።
30“የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ከክፉ ነገር በቀር በፊቴ አንዳች በጎ ነገር አልሠሩም፤ በርግጥም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ አስቈጡኝ፤ ይላል እግዚአብሔር31ይህች ከተማ፣ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከፊቴ እንዳስወግዳት ቍጣዬንና መዓቴን አነሣሥታለች፤ 32የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ፣ እነርሱ፣ ነገሥታታቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸው፣ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ባደረጉት ክፋት ሁሉ አስቈጡኝ። 33ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፤ ደጋግሜ ባስተምራቸውም አይሰሙም፤ ተግሣጽም አይቀበሉም። 34ስሜ በተጠራበት ቤት አስጸያፊ ጣዖታቸውን አቆሙ፤ አረከሱትም። 35ወንዶችና ሴቶች#32፥35 ወይም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያሳልፉ ዘንድ ልጆቻቸውን ለሞሎክ ይሠዉ ዘንድ በሄኖም ሸለቆ ለበኣል መስገጃ ኰረብቶችን ሠሩ፤ ነገር ግን ይሁዳን ኀጢአት ለማሠራት እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝሁም፤ ከቶም አላሰብሁም።
36“ ‘በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፋ ትሰጣለች’ ስላልሃት ስለዚህች ከተማ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ 37‘በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ በሰላምም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ። 38እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 39ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው ዘወትር ይፈሩኝ ዘንድ፣ አንድ ልብ አንድም ሐሳብ እሰጣቸዋለሁ። 40መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ። 41ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።’
42እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት እንዳመጣሁ እንደዚሁ ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ። 43እናንተም፣ “ለባቢሎናውያን ዐልፋ ስለ ተሰጠች፣ ሰውና እንስሳ የማይኖሩባት ባድማ ናት” ባላችኋት በዚህች ምድር እንደ ገና መሬት ይገዛል። 44ምርኳቸውን ስለምመልስላቸው#32፥44 ወይም ከምርኮ ስለምመልሳቸው በብንያም አገር፣ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች፣ በይሁዳ ከተሞችና በተራራማው አገር ከተሞች፣ በምዕራብ ተራሮች ግርጌና በኔጌብ ባሉ ከተሞች፣ መሬት በጥሬ ብር ይገዛል፤ ውሉም ተፈርሞ፤ በምስክሮች ፊት ይታሸጋል፤’ ይላል እግዚአብሔር።”

Currently Selected:

ኤርምያስ 32: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ