በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፣ እግዚአብሔር ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው፤ ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው፤ እነዚህም አሕዛብ ዐምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፣ ከነዓናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማት መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነዚህ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለቀደሙ አባቶቻቸው የሰጠውን ትእዛዞች ማክበር አለማክበራቸውን ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛ እንዲሆኑ እዚያው የቀሩ ነበሩ። ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋራ ዐብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክታቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔር አምላካቸውንም ረሱ፤ የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አመለኩ። እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኵስርስቴም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ ግን የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ በርሱ ላይ ወረደ፤ የእስራኤል መስፍን ሆኖ ወደ ጦርነትም ወጣ። እግዚአብሔር የአራም ንጉሥ ኵስርስቴምን አሳልፎ ስለ ሰጠው ድል አደረገ። የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች። እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ይህን በማድረጋቸውም እግዚአብሔር የሞዓብ ንጉሥ ዔግሎን በእስራኤል ላይ እንዲበረታባቸው አደረገ። እርሱም አሞናውያንንና አማሌቃውያንን ካስተባበረ በኋላ እስራኤልን ወግቶ የዘንባባ ዛፎች ከተማ የሆነችውን ኢያሪኮን ያዙ። እስራኤላውያንም ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን ዐሥራ ስምንት ዓመት ተገዘሉት። እስራኤላውያን እንደ ገና ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ግራኙን ናዖድን ነጻ እንዲያወጣቸው አስነሣው። እስራኤላውያን ናዖድን ግብር አስይዘው ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎን ላኩት። እርሱም በሁለት በኩል ስለታም የሆነና አንድ ክንድ ተኩል ርዝመት ያለው ሰይፍ አዘጋጅቶ በልብሱ ውስጥ በቀኝ ጭኑ ላይ አሰረው። ግብሩንም ወፍራም ለነበረው ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን አቀረበ፤ ናዖድም ግብሩን ካቀረበ በኋላ፣ ግብር ተሸክመው የመጡት ሰዎች ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ። እርሱ ራሱ ግን ጌልገላ አጠገብ ድንጋዮች ተጠርበው ከሚወጡበት አካባቢ ሲደርስ ወደ ኋላ በመመለስ ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በምስጢር የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። ንጉሡም፣ “ጸጥታ” ሲል፤ አጠገቡ የነበሩት አገልጋዮች በሙሉ ትተዉት ወጡ። ንጉሡ ሰገነት ላይ ባለው ነፋሻ ዕልፍኝ ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ሳለ ናዖድ ቀረብ ብሎ፣ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ያመጣሁት መልእክት አለኝ” አለው፤ ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሣ። ናዖድ ግራ እጁን ሰደድ በማድረግ ሰይፉን ከደበቀበት ከቀኝ ጭኑ መዝዞ በንጉሡ ሆድ ሻጠው። እጀታው ሳይቀር ሰይፉ እንዳለ ሆዱ ውስጥ ገባ፤ ስለቱም በጀርባው ወጣ፤ ሞራም ስለቱን ሸፈነው፤ ናዖድ ሰይፉን ስላልነቀለው አንጀቱ ተዘረገፈ። ከዚያም በኋላ ናዖድ በዕልፍኙ መግቢያ ወጣ፤ የዕልፍኙንም በር በንጉሡ ላይ ዘግቶ ቈለፈው። ናዖድ ከሄደ በኋላ፣ የንጉሡ አገልጋዮች ሲመጡ፣ የዕልፍኙ በር ተቈልፎ አገኙት፤ እነርሱም፣ “በውስጠኛው ክፍል እየተጸዳዳ ይሆናል” አሉ፤ እስኪደክማቸውም ድረስ ጠበቁ፤ ነገር ግን ንጉሡ የዕልፍኙን በሮች ባለመክፈቱ ቍልፍ ወስደው ከፈቱ፤ በዚያም ጌታቸው ሞቶ፣ በወለሉም ላይ ተዘርግቶ አገኙት። የንጉሡ አገልጋዮች በዕልፍኙ በር ላይ ቆመው ሲጠባበቁ ናዖድ ርቆ ሄደ፤ ድንጋዮች ተጠርበው በሚወጡበት በኩል ወደ ሴርታይም አመለጠ። እዚያም እንደ ደረሰ፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ እስራኤላውያንም በርሱ መሪነት ከኰረብታው ላይ ዐብረውት ወረዱ።
መሳፍንት 3 ያንብቡ
ያዳምጡ መሳፍንት 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሳፍንት 3:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች