የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ያዕቆብ 3:1-12

ያዕቆብ 3:1-12 NASV

ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር፣ እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም፣ የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች። ማንኛውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣል። ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህ ሊሆን አይገባም። ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ፤ በለስ ወይራን ወይንም በለስን ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም።