ኢሳይያስ 3:1-15

ኢሳይያስ 3:1-15 NASV

እነሆ፤ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፉንና ርዳታውን፣ የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤ ጀግናውንና ተዋጊውን፣ ፈራጁንና ነቢዩን፣ አስማተኛውንና ሽማግሌውን፣ የዐምሳ አለቃውንና ባለማዕርጉን፣ አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለሙያ፣ ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል። “ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤ ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል።” ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤ ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፣ ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፣ ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል። ሰውም በአባቱ ቤት ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፣ “አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤ ይህንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ!” ይለዋል። እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኔ መፍትሒ አልሆንም፤ በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤ የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል። ኢየሩሳሌም ተንገዳግዳለች፤ ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚቃወም፣ የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና። የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤ አይደብቁትምም፤ ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ፣ ወዮላቸው! ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና። በደለኞች ወዮላቸው! ጥፋት ይመጣባቸዋል! የእጃቸውን ያገኛሉና። ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤ ሴቶችም ይገዟቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤ ከመንገድህም መልሰውሃል። እግዚአብሔር በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጧል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቷል። እግዚአብሔር፣ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋራ እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤ ሕዝቤን በችግር ስታደቅቁት፣ የድኾችንም ፊት በሐዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?” ይላል ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።