ዕብራውያን 8:7-13

ዕብራውያን 8:7-13 NASV

የመጀመሪያው ኪዳን ምንም ጕድለት ባይገኝበት ኖሮ፣ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል፤ “ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ፣ አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ። ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ ምክንያቱም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑም፤ እኔም ከእነርሱ ዘወር አልሁ፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ከእንግዲህ ማንም ሰው ጎረቤቱን ወይም ወንድሙን፣ ‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ምክንያቱም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ፣ ሁሉም ያውቁኛል። በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስብም።” ይህን ኪዳን፣ “አዲስ” በማለቱ የፊተኛውን ኪዳን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ያረጀ ያፈጀው የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።