ዕብራውያን 8:7-13
ዕብራውያን 8:7-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፊተኛይቱ ያለ ነቀፋ ብትሆን ኖሮ ሁለተኛይቱን ባልፈለገም ነበር። ነገር ግን እነርሱን ነቅፎ እንዲህ አለ፥ “እነሆ፥ ለቤተ እስራኤልና ለቤተ ይሁዳም አዲስ ኪዳን የምሠራበት ዘመን ይመጣል ይላል እግዚአብሔር። እጃቸውን ይዤ ከምድረ ግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ ለአባቶቻቸው እንደ ገባሁት እንደዚያ ያለ ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልኖሩምና፤ እኔም ቸል ብያቸዋለሁና” ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ዘመናት በኋላ ለቤተ እስራኤል የምገባው ቃል ይህ ነው፦ ሕጌን በልባቸው አሳድራለሁ፤ በሕሊናቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል ይላል እግዚአብሔር። እንግዲህ አንዱ ሌላውን አያስተምርም፤ ወንድምም ወንድሙን እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። ዐመፃቸውን እምራቸዋለሁና ኀጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም።” አዲስ ትእዛዝ በማለቱ የቀደመችቱን አስረጃት፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ለጥፋት የቀረበ ነው።
ዕብራውያን 8:7-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የመጀመሪያው ኪዳን ምንም ጕድለት ባይገኝበት ኖሮ፣ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል፤ “ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ፣ አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ። ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ ምክንያቱም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑም፤ እኔም ከእነርሱ ዘወር አልሁ፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ከእንግዲህ ማንም ሰው ጎረቤቱን ወይም ወንድሙን፣ ‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ምክንያቱም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ፣ ሁሉም ያውቁኛል። በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስብም።” ይህን ኪዳን፣ “አዲስ” በማለቱ የፊተኛውን ኪዳን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ያረጀ ያፈጀው የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።
ዕብራውያን 8:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና፦ እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤ ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ። ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል። እያንዳንዱም ጐረቤቱን እያንዳንዱም ወንድሙን፦ ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም። አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።
ዕብራውያን 8:7-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ነቀፋ የሌለው ሆኖ ቢገኝ ኖሮ ሁለተኛው ቃል ኪዳን ባላስፈለገ ነበር። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ነቀፋ መኖሩን በማመልከት እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል” ይላል ጌታ። ይህም ቃል ኪዳን እጃቸውን ይዤ ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እነርሱ በቃል ኪዳኔ ስላልጸኑ እኔም ችላ አልኳቸው ይላል ጌታ። “እነሆ፥ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን የሚከተለው ነው ይላል ጌታ፤ እኔ ሕጌን በአእምሮአቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ ጎረቤቱን ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ሁሉም ያውቀኛል፤ በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም።” እንግዲህ “አዲስ ቃል ኪዳን” ሲል የፊተኛውን ቃል ኪዳን አሮጌ አድርጎታል ማለት ነው፤ ስለዚህ የተሠራበትና አሮጌው ነገር ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።
ዕብራውያን 8:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፊተኛው ኪዳን ጉድለት ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ጉድለት አግኝቶባቸዋልና እንዲህ ይላቸዋል፦ “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምመሠርትበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ ከግብጽ ምድር ለማውጣት እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና እኔም ቸል አልኳቸው፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል። እያንዳንዱም ‘ጌታን እወቅ፥’ ብሎ ጐረቤቱን ወይም ወንድሙን አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስብም።” “አዲስ” በሚል ጊዜ ፊተኛውን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ጊዜው ያለፈበትና አሮጌው ነገር ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።