ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል። ይህኛው ካህን ግን ስለ ኀጢአት አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤ ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤ “ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእነርሱ ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።” ደግሞም፣ “ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣ ከእንግዲህ አላስብም” ይላል። እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው። በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን፣ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ። እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
ዕብራውያን 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕብራውያን 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕብራውያን 10:11-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos