ዕብራውያን 10:11-25

ዕብራውያን 10:11-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሊቀ ካህ​ና​ትም ሁሉ ዘወ​ትር እያ​ገ​ለ​ገለ ይቆም ነበር፤ ፈጽሞ ኀጢ​አት ማስ​ተ​ስ​ረይ የማ​ይ​ቻ​ላ​ቸ​ውን እነ​ዚ​ያን መሥ​ዋ​ዕ​ቶች ብቻም ይሠዋ ነበር። እርሱ ግን ስለ ኀጢ​አት አን​ድን መሥ​ዋ​ዕት ለዘ​ለ​ዓ​ለም አቅ​ርቦ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቀኝ ተቀ​መጠ። እን​ግ​ዲህ ጠላ​ቶቹ ከእ​ግሩ በታች እስ​ኪ​ወ​ድቁ ድረስ ይጠ​ብ​ቃል። ለሚ​ቀ​ደ​ሱ​ትም ለዘ​ለ​ዓ​ለም የም​ት​ሆን አን​ዲት መሥ​ዋ​ዕ​ትን ሠዋ። መን​ፈስ ቅዱ​ስም ምስ​ክ​ራ​ችን ነው። “ከእ​ነ​ዚያ ወራ​ቶች በኋላ የም​ገ​ባ​ላ​ቸው ኪዳን ይህቺ ናት ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፤ ሕጌን በል​ባ​ቸው አኖ​ረ​ዋ​ለሁ፤ በል​ቡ​ና​ቸ​ውም እጽ​ፈ​ዋ​ለሁ ካለ በኋላ። ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲህ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ው​ንና በደ​ላ​ቸ​ውን ደግሜ አላ​ስ​ብ​ባ​ቸ​ውም” ብሏል። እን​ዲ​ህም ኀጢ​አት የሚ​ሰ​ረይ ከሆነ፥ እን​ግ​ዲህ ወዲህ ስለ ኀጢ​አት መሥ​ዋ​ዕት አያ​ስ​ፈ​ል​ግም። እን​ግ​ዲህ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ደም ወደ መቅ​ደስ ለመ​ግ​ባት ባለ​ሙ​አ​ል​ነት አለን። በሥ​ጋው መጋ​ረጃ በኩል የሕ​ይ​ወ​ት​ንና የጽ​ድ​ቅን መን​ገድ ፈጽሞ አድ​ሶ​ል​ና​ልና። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት ታላቅ ካህን አለን። እን​ግ​ዲህ ከክፉ ሕሊና ለመ​ን​ጻት ልባ​ች​ንን ተረ​ጭ​ተን፥ ሰው​ነ​ታ​ች​ን​ንም በጥሩ ውኃ ታጥ​በን በተ​ረ​ዳ​ን​በት እም​ነት በቅን ልብ እን​ቅ​ረብ። እን​ግ​ዲህ የማ​ይ​ና​ወ​ጠ​ውን የተ​ስ​ፋ​ች​ንን እም​ነት እና​ጽና፤ ተስፋ የሰጠ እርሱ የታ​መነ ነውና። በፍ​ቅ​ርና በበጎ ምግ​ባ​ርም ከባ​ል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ችን ጋር እን​ፎ​ካ​ከር። ሌሎች ልማድ አድ​ር​ገው እንደ ያዙት ማኅ​በ​ራ​ች​ንን አን​ተው፤ እርስ በር​ሳ​ችን እን​መ​ካ​ከር እንጂ፤ ይል​ቁ​ንም ቀኑ ሲቀ​ርብ እያ​ያ​ችሁ አብ​ል​ጣ​ችሁ ይህን አድ​ርጉ።

ዕብራውያን 10:11-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል። ይህኛው ካህን ግን ስለ ኀጢአት አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤ ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤ “ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእነርሱ ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።” ደግሞም፣ “ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣ ከእንግዲህ አላስብም” ይላል። እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው። በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን፣ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ። እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።

ዕብራውያን 10:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ፥ ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።

ዕብራውያን 10:11-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እያንዳንዱ ካህን ኃጢአትን ማስወገድ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ዘወትር እያቀረበ በየቀኑ ቆሞ ያገለግላል። ክርስቶስ ግን ለሁልጊዜ የሚሆነውን አንዱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦአል። ከእንግዲህ ወዲህ ጠላቶቹ በሥልጣኑ ሥር እስኪሆኑ ድረስ ይጠባበቃል፤ ይህም የሆነው እነዚያን የተቀደሱትን በአንዱ መሥዋዕት አማካይነት ለዘለዓለም ፍጹሞች ስለ አደረጋቸው ነው። መንፈስ ቅዱስም በዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ፥ “ከእነዚያ ቀኖች በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሮአቸውም እጽፈዋለሁ።” ቀጥሎም “ኃጢአታቸውንና ክፉ ሥራቸውን ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” ይላል። ስለዚህ ኃጢአት ሁሉ ከተደመሰሰ በኋላ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ደም አማካይነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት የሚያስችለንን መተማመኛ አግኝተናል፤ የምንገባውም በመጋረጃው፥ ማለትም በሥጋው አማካይነት በከፈተልን በአዲሱና ሕያው በሆነው መንገድ ነው። በእግዚአብሔር ቤት ላይ ሥልጣን ያለው ትልቅ ካህን አለን። ስለዚህ ከክፉ ኅሊና እንድንነጻ ልባችንን ተረጭተን፥ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፥ ቅን ልብና እውነተኛ እምነት ይዘን ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። የተስፋውን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ አሁን አምነን የምንመሰክረውን ተስፋ ሳናወላውል አጥብቀን እንያዝ። በፍቅርና በመልካም ሥራ ነቅተን እንድንኖር አንዱ ሌላውን ያሳስበው፤ ዘወትር እየተገናኘን እርስ በርሳችን እንበረታታ እንጂ አንዳንዶች ማድረግ እንደ ለመዱት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም የጌታ መምጫ ቀን መቃረቡን እያስታወሳችሁ ይህን ነገር በይበልጥ አድርጉ።

ዕብራውያን 10:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሊቀ ካህናትም ሁሉ በየዕለቱ እያገለገለ እነዚያን ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን መሥዋዕቶች ደጋግሞ ለማቅረብ ይቆማል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድ መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤ አሁን ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ እንዲህ በማለት፦ “ከነዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ “በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ፥ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ፤” እንደዚሁም፥ “ኀጢአታቸውንና ዐመጻቸውንም ደግሜ አላስብም፤” ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የለም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ወደ ቅድስት ለመግባት በኢየሱስ ደም ድፍረት ስላለን፥ በአዲስና በሕያው መንገድ በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል ተከፍቶልን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተንና ሰውነታችንን በንጹህ ውሃ ታጥበን፥ በቅን ልብ በፍጹም እምነት እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና፥ ተስፋ የሚሰጠንን ምስክርነት ያለመናወጥ በጽናት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተሳሰብ፤ አንዳንዶችም ልምድ አድርገው እንደያዙት፥ መሰብሰባችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር፤ ይልቁንም የቀኑን መቅረብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።