የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 7:13-24

ዘፍጥረት 7:13-24 NASV

በዚያ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ። ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ ዐብረዋቸው ገቡ። የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጥረታት በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ። ከሕያዋንም ፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከውጭ ዘጋበት። የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ 7 ሜትር ያህል ከፍ አለ። በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጥረታት፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ። በአፍንጫቸው የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በየብስ የነበሩ ፍጥረታት ሁሉ ሞቱ። ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፉ፤ ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና የሰማይ ወፎች ከምድር ላይ ጠፉ፤ ኖኅና ከርሱ ጋራ በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ። ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ ዐምሳ ቀን ቈየ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}