ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፣ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ እነሆ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ሰባት ላሞች ሲውጧቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬአቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬአቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር። በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብጽ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፤ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጕምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም። በዚያ ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጕም ነበረው። በዚያ ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋራ እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍችውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።”
ዘፍጥረት 41 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 41
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 41:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች