ዘፍጥረት 39:6-15

ዘፍጥረት 39:6-15 NASV

ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በቀር፣ ማንኛውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለች፤ አፍ አውጥታም፣ “ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከርሷ ጋራ መተኛት ይቅርና ዐብሯትም መሆን አልፈቀደም። አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣ የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሯል! ሊተኛኝ ወደ እኔ ገባ፤ እኔም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኽሁ፤ ለርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}