ዘፍጥረት 39:6-15

ዘፍጥረት 39:6-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ያለ​ው​ንም ሁሉ ለዮ​ሴፍ በእጁ አስ​ረ​ከ​በው፤ ከሚ​በ​ላ​ውም እን​ጀራ በቀር ምንም የሚ​ያ​ው​ቀው አል​ነ​በ​ረም። ዮሴ​ፍም መልኩ ያማረ፥ ፊቱም እጅግ የተ​ዋበ ነበር። ከዚ​ህም በኋላ እን​ዲህ ሆነ፤ የጌ​ታው ሚስት በዮ​ሴፍ ላይ ዐይ​ን​ዋን ጣለ​ች​በት፤ “ከእ​ኔም ጋር ተኛ” አለ​ችው። እር​ሱም እንቢ አለ፤ ለጌ​ታ​ውም ሚስት እን​ዲህ አላት፥ “እነሆ፥ ጌታዬ በቤቱ ያለ​ውን ሁሉ ለእኔ በእጄ አስ​ረ​ክ​ቦ​ኛል፤ በቤቱ ያለ​ው​ንም ምንም የሚ​ያ​ው​ቀው የለም፤ በዚህ ቤት ከእኔ የሚ​በ​ልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ​ሆ​ንሽ ከአ​ንቺ በቀር ያል​ሰ​ጠኝ ነገር የለም፤ እን​ዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደ​ር​ጋ​ለሁ? በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት እን​ዴት ኀጢ​አ​ትን እሠ​ራ​ለሁ?” ይህ​ንም ነገር በየ​ዕ​ለቱ ለዮ​ሴፍ ትነ​ግ​ረው ነበር፤ እር​ሱም ከእ​ር​ስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ፥ ከእ​ር​ስ​ዋም ጋር ይሆን ዘንድ አል​ሰ​ማ​ትም። በአ​ን​ዲ​ትም ቀን እን​ዲህ ሆነ፤ በዚያ ቀን ሥራ​ውን እን​ዲ​ሠራ ዮሴፍ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤ​ትም ውስጥ ከቤተ ሰዎች ማንም አል​ነ​በ​ረም። ልብ​ሱን ይዛ፥ “ና ከእኔ ጋር ተኛ” አለ​ችው፤ እር​ሱም ልብ​ሱን በእ​ጅዋ ትቶ​ላት ሸሸ፤ ወደ ውጭም ወጣ። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ልብ​ሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ በአ​የች ጊዜ፥ የቤ​ቷን ሰዎች ወደ እር​ስዋ ጠርታ እን​ዲህ ብላ ነገ​ረ​ቻ​ቸው፥ “እዩ፤ ይህ ዕብ​ራዊ ባርያ በእኛ እን​ዲ​ሣ​ለቅ አመ​ጣ​ብን፤ እርሱ ወደ እኔ ገብቶ ከእኔ ጋር ተኚ አለኝ፤ እኔም ድም​ፄን ከፍ አድ​ርጌ ጮኽሁ፤ ድም​ፄ​ንም ከፍ አድ​ርጌ እንደ ጮኽሁ ቢሰማ፥ ልብ​ሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ፤ ወደ ውጭም ወጣ።”

ዘፍጥረት 39:6-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በቀር፣ ማንኛውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለች፤ አፍ አውጥታም፣ “ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከርሷ ጋራ መተኛት ይቅርና ዐብሯትም መሆን አልፈቀደም። አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣ የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሯል! ሊተኛኝ ወደ እኔ ገባ፤ እኔም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኽሁ፤ ለርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”

ዘፍጥረት 39:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴርም ፊቱ መልከ መልካምን ውብ ነበረ። ከዚህም በኍላ እንዲህ ሆነ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች፦ ከእኔም ጋር ተኛ አለችው። እርሱም እንቢ አለ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት፦ እነሆ ጌታዬ በቤት ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የስም ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፋ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ? ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም። እንዲህም ሆነ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ ወደ ቤቱ ገባ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም። ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ። እንዲህም ሆን ልብሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ ባየች ጊዜ የቤትዋን ሰዎች ወደ እርስዋ ጠርታ እንዲህ ብላ ነገረቻቸው፦ እዮ ዕብራዊው ሰው በእኛ እንዲሣለቅ አግብቶብናል፤ እርሱ ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ፤ ድምፄንም ከፍ አድርግው እንደ ጮኽሁ ቢስማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።

ዘፍጥረት 39:6-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስለዚህ ጶጢፋር ያለውን ንብረት ሁሉ በዮሴፍ ቊጥጥር ሥር አደረገ፤ ጶጢፋር ከሚመገበው ምግብ በስተቀር የሚያውቀው ምንም ነገር አልነበረም። ዮሴፍ ቁመናው የተስተካከለ መልከ መልካም ሰው ነበር። ከጊዜ በኋላ የጌታው ሚስት ዮሴፍን ተመልክታ ስለ አፈቀረችው፥ “ና ከእኔ ጋር አብረን እንተኛ” አለችው። እርሱ ግን ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሁሉንም ነገር በእኔ ኀላፊነት ሥር ስላደረገ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ንብረት ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውን ንብረት ሁሉ እንዳስተዳድርለት በዐደራ ለእኔ ሰጥቶኛል። ጌታዬ በዚህ ቤት ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት የለውም፤ ከአንቺ በቀር በእኔ ቊጥጥር ሥር ያላደረገው ምንም ነገር የለም፤ ይኸውም ሚስቱ ስለ ሆንሽ ነው፤ ታዲያ ይህን አስከፊ ኃጢአት በመፈጸም እግዚአብሔርን እንዴት አሳዝናለሁ?” እርስዋም ይህንኑ ጉዳይ በየቀኑ ትነግረው ነበር፤ ዮሴፍ ግን አብሮአት መተኛት ወይም በአጠገቧ ለመገኘት አልፈለገም። ከዕለታት አንድ ቀን ዮሴፍ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤት ሲገባ በቤት ውስጥ አንድም ሠራተኛ አልነበረም። በዚያን ጊዜ የጌታው ሚስት ልብሱን ይዛ “ከእኔ ጋር ተኛ” አለችው፤ እርሱ ግን ልብሱን እጅዋ ላይ ትቶላት ከቤት ሸሽቶ ወጣ። እርስዋም ልብሱን በእጅዋ ላይ ትቶ ከቤት ሸሽቶ መውጣቱን በተመለከተች ጊዜ፥ አገልጋዮችዋን ጠርታ እንዲህ አለቻቸው፤ “እነሆ፥ ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ ሊያዋርደን ነበር፤ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊደፍረኝ ሞከረ፤ እኔ ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽኩ። ርዳታ ለማግኘትም መጮኼን በሰማ ጊዜ ልብሱን አጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።”

ዘፍጥረት 39:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፥ ማናቸውንም ጉዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፥ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፥ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጉተውም፥ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛቱ ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም። አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፥ የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሮአል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤ ለእርዳታ መጮኼን ሲሰማም፥ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።”