ዘፍጥረት 31:2-21

ዘፍጥረት 31:2-21 NASV

የላባ አመለካከት ከቀድሞው የተለወጠበት መሆኑንም ያዕቆብ ተረዳ። እግዚአብሔርም ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህና ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ካንተ ጋራ እሆናለሁ” አለው። ስለዚህም ያዕቆብ መንጎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ፣ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ አልተለየኝም፤ መቼም ባለኝ ዐቅም አባታችሁን ማገልገሌ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም። አባታችሁ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጐዳኝ እግዚአብሔር አልፈቀደለትም። እርሱ፣ ‘ደመወዝህ ዝንጕርጕሮቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ደመወዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ። “እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት፣ የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች መልካቸው፣ ሽመልመሌ፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ዐይኔን አንሥቼ በሕልሜ አየሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ፣ ‘ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፣ ‘እነሆ አለሁኝ’ አልሁት። እርሱም ‘መንጎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸው፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ቀና ብለህ ተመልከት፤ ላባ በአንተ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ሁሉ አይቻለሁና፤ የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅና ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ።” ራሔልና ልያም እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “ከአባታችን ሀብት የምናገኘው ምን ውርስ አለ? እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? ደግሞም እኮ እኛን ሸጦናል፤ የተሸጥንበትንም ዋጋ ራሱ በልቶታል። እግዚአብሔር ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የነገረህን ሁሉ አድርግ።” ከዚያም ያዕቆብ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋራ ከብቶቹን በሙሉ ወደ ፊት አስቀደመ፤ ወደ አባቱም ወደ ይሥሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጕዞውን ቀጠለ። ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ሳለ፣ ራሔል የአባቷን ቤት የጣዖታት ምስል ሰረቀች። ያዕቆብም ቢሆን፣ መኰብለሉን ለሶርያዊው ለላባ ሳይገልጥለት በመቅረቱ አታልሎታል። ያዕቆብ የርሱ የሆነውን ሁሉ ይዞ፣ የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኰረብታማው አገር፣ ወደ ገለዓድ አመራ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}