የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 31

31
ያዕቆብ ከላባ ቤት ኰበለለ
1የላባ ወንዶች ልጆች፣ “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት እንዳለ ወስዶታል፤ ይህ ሁሉ እርሱ ያካበተውም ሀብት ከአባታችን የተገኘ ነው” እያሉ ሲያወሩ ያዕቆብ ሰማ። 2የላባ አመለካከት ከቀድሞው የተለወጠበት መሆኑንም ያዕቆብ ተረዳ።
3 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህና ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ” አለው።
4ስለዚህም ያዕቆብ መንጎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ፣ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ 5እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም) አልተለየኝም፤ 6መቼም ባለኝ ዐቅም አባታችሁን ማገልገሌ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም። 7አባታችሁ ደሞዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጐዳኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አልፈቀደለትም። 8እርሱ፣ ‘ደመወዝህ ዝንጕርጕሮቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ደመወዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤ 9ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ።
10“እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት፣ የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች መልካቸው፣ ሽመልመሌ፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ዐይኔን አንሥቼ በሕልሜ አየሁ። 11የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መልአክ፣ ‘ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፣ ‘እነሆ አለሁኝ’ አልሁት። 12እርሱም ‘መንጎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸው፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ቀና ብለህ ተመልከት፤ ላባ በአንተ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ሁሉ አይቻለሁና፤ 13የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ (ኤል) እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅና ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ።”
14ራሔልና ልያም እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “ከአባታችን ሀብት የምናገኘው ምን ውርስ አለ? 15እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? ደግሞም እኮ እኛን ሸጦናል፤ የተሸጥንበትንም ዋጋ ራሱ በልቶታል። 16እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የነገረህን ሁሉ አድርግ።”
17ከዚያም ያዕቆብ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ 18በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋር ከብቶቹን በሙሉ ወደ ፊት አስቀደመ፤ ወደ አባቱም ወደ ይስሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጕዞውን ቀጠለ።
19ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ሳለ፣ ራሔል የአባቷን ቤት የጣዖታት ምስል ሰረቀች።
20ያዕቆብም ቢሆን፣ መኰብለሉን ለሶርያዊው ለላባ ሳይገልጥለት በመቅረቱ አታልሎታል። 21ያዕቆብ የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይዞ፣ የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኰረብታማው አገር፣ ወደ ገለዓድ አመራ።
ላባ ያዕቆብን ተከታተለው
22የያዕቆብ መኰብለል ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው። 23ላባ ዘመዶቹን ይዞ ተነሣ፤ ያዕቆብንም ሰባት ቀን ተከታትሎ ገለዓድ በተባለ ኰረብታማ አገር ደረሰበት። 24ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሶርያዊው ለላባ በሕልም ተገልጦ፣ “ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ፣ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው።
25ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኰረብታማ አገር ድንኳኑን ተክሎ ሳለ፣ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም በዚያው ሰፈሩ። 26ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ምን ማድረግህ ነው? አታልለኸኛል፤ ልጆቼን የጦር ምርኮኛ ይመስል አካልበህ ወሰድሃቸው። 27ለመሆኑ ለምን ተደብቀህ ሄድህ? ለምንስ አታለልኸኝ? ብትነግረኝ ኖሮ፣ በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና አልሸኝህም ነበር? 28የልጆቼን ልጆችና ልጆቼንም ስሜ ብሰናበት ምን ነበረበት? የሠራኸው የጅል ሥራ ነው። 29ልጐዳችሁ እችል ነበር፤ ዳሩ ግን ባለፈው ሌሊት የአባታችሁ አምላክ (ኤሎሂም) ‘ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ አለኝ። 30አንተ ወደ አባትህ ቤት ለመመለስ ስለ ናፈቅህ ሄደሃል፤ ነገር ግን የቤቴን የጣዖት ምስል የሰረቅኸው ለምንድን ነው?”
31ያዕቆብም ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶች ልጆችህን በኀይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው። 32ነገር ግን ከእኛ መካከል የአንተን የጣዖታት ምስል ደብቆ የተገኘ ሰው ካለ ይሙት። ያንተ የሆነ አንዳች ነገር ከኔ ዘንድ ቢገኝ፣ አንተው ራስህ ዘመዶቻችን ባሉበት ፈልግና ውሰድ።” ይህን ሲል፣ ራሔል የጣዖታቱን ምስል መስረቋን ያዕቆብ አያውቅም ነበር።
33ላባም ወደ ያዕቆብ፣ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ደንገጡሮቿ ድንኳኖች ገባ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም። ከልያ ድንኳን ከወጣ በኋላ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። 34ራሔል የጣዖታቱን ምስል ከግመሏ ኮርቻ ሥር ሸሽጋ፣ በላዩ ተቀምጣበት ነበር፤ ላባም ድንኳኑን አንድ በአንድ በርብሮ ምንም ሊያገኝ አልቻለም።
35ራሔልም አባቷን፣ “በፊትህ ተነሥቼ መቆም ስላልቻልሁ፣ ጌታዬ አትቈጣ፤ የወር አበባዬ መጥቶ ነው።” አለችው፤ ስለዚህ በረበረ፤ የጣዖታቱን ምስል ግን ማግኘት አልቻለም።
36በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቈጣ፤ ላባንም እንዲህ ሲል ወቀሠው፤ “እስቲ ወንጀሌ ምንድን ነው? ይህን ያህል የምታሳድደኝ ኀጢአቴ ምን ቢሆን ነው? 37ዕቃዬን አንድ በአንድ በርብረሃል፤ ታዲያ፣ የአንተ ሆኖ ያገኘኸው ዕቃ የትኛው ነው? ካለ፣ እስቲ በአንተም በእኔም ዘመዶች ፊት አቅርብና እነርሱ ያፋርዱን።
38“ሃያ ዓመት አብሬህ ኖሬአለሁ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከመንጋህ አንድ ጠቦት እንኳ አልበላሁም። 39አውሬ የሰበረውንም ቢሆን እተካ ነበር እንጂ፣ ትራፊውን ለምልክትነት አምጥቼ አላውቅም፤ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቁትን ሁሉ ስታስከፍለኝ ኖረሃል። 40ቀን በሐሩር ሌሊት በቍር ተቃጠልሁ፤ እንቅልፍም በዐይኔ አልዞር አለ፤ 41ሃያ ዓመት በቤትህ የኖርሁት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ዐሥራ አራት ዓመት ለሁለቱ ልጆችህ ብዬ አገለገልሁ፤ ስድስት ዓመት ስለ መንጋዎችህ ስል አገለገልሁ፤ ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋውጠህብኛል። 42የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም)፣ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም)፣ የይስሐቅም ፍርሀት ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ሰድደኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን መከራዬን አይቶ፣ ልፋቴን ተመልክቶ ትናንት ሌሊት ገሠጸህ።”
43ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶቹም፣ ልጆቹም የእኔው ልጆች ናቸው፣ መንጎቹም ቢሆኑ የራሴ ናቸው። ታዲያ፣ በእነዚህ ሴቶች ልጆቼና በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ? 44በል አሁን ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ኪዳኑም በአንተና በእኔ መካከል ምስክር ይሁን።”
45ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤ 46ከዚያም ዘመዶቹን፣ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ፤ በክምሩም አጠገብ ምግብ በሉ። 47ላባም ክምር ድንጋዩን ይጋርሠሀዱታ#31፥47 ይጋርሠሀዱታ የሚለው ቃል በአረማይክ የኪዳን ክምር ድንጋይ ማለት ነው። ብሎ ጠራው፤ ያዕቆብ ደግሞ ገለዓድ#31፥47 ገለዓድ የሚለው ቃል በዕብራይስጥ የኪዳን ክምር ድንጋይ ማለት ነው። አለው።
48ላባም “ይህ ክምር ድንጋይ በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለው። ገለዓድ ተብሎ የተጠራውም በዚሁ ምክንያት ነው፤ 49ደግሞም ምጽጳ#31፥49 ምጽጳ የሚለው ቃል መጠበቂያ ማማ ማለት ነው። ተባለ፤ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሏልና፤ “እኛ በተለያየን ጊዜ፣ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ታዛቢ ሆኖ ይቁም። 50ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም ሌሎች ሚስቶች በላያቸው ላይ ብታገባ፣ ማንም ከእኛ ጋር ባይኖርም እንኳ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በአንተና በእኔ መካከል ምስክር መሆኑን አትርሳ።”
51ደግሞም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ክምር ድንጋዩ እነሆ፤ በአንተና በእኔ መካከል ያቆምሁትም ሐውልት እነሆ፤ 52ይህን ክምር ድንጋይ ዐልፌ አንተን ለማጥቃት ላልመጣ፣ አንተም ይህን ክምር ድንጋይና ይህን ሐውልት ዐልፈህ እኔን ለማጥቃት ላትመጣ፣ ይህ ክምር ድንጋይ ምስክር ነው፤ ይህም ሐውልት ምስክር ነው። 53የአብርሃም አምላክ፣ የናኮር አምላክ፣ የአባታቸውም አምላክ (ኤሎሂም) በመካከላችን ይፍረድብን”።
ስለዚህ ያዕቆብ በአባቱ በይስሐቅ ፍርሀት ማለ። 54ያዕቆብ በኰረብታማው አገር ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው፤ እነርሱም ከበሉ በኋላ እዚያው ዐደሩ።
55በማግስቱም ማለዳ ላባ የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 31: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ