ሕዝቅኤል 11
11
በእስራኤል መሪዎች ላይ የተላለፈ ፍርድ
1መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፤ ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር አመጣኝ። በበሩም መግቢያ ላይ ሃያ አምስት ሰዎች ነበሩ፤ በእነርሱም መካከል የሕዝቡን መሪዎች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስን ልጅ ፈላጥያንን አየሁ። 2እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ክፋትን የሚያቅዱና በዚህችም ከተማ ላይ ተንኰልን የሚመክሩ ናቸው። 3እነርሱም፣ ‘ቤቶች የሚሠሩበት ጊዜ ቅርብ አይደለምን?#11፥3 ወይም ቤቶችን ለመሥራት ጊዜው አሁን አይደለም ይህች ከተማ ድስት ናት፤ እኛም ሥጋ ነን’ ብለዋል። 4ስለዚህ ትንቢት ተናገርባቸው፤ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር።”
5 የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዬ ወረደ፤ እንዲህም አለኝ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እናንተ እንዲህ ብላችኋል፤ እኔ ግን የልባችሁን ሐሳብ ዐውቃለሁ። 6በዚህች ከተማ ብዙ ሰው ገድላችኋል፤ መንገዶቿንም ሬሳ በሬሳ አድርጋችኋል።’
7“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በዚያ የጣላችኋቸው ሬሳዎች እነርሱ ሥጋ ናቸው፤ ይህችም ከተማ ድስት ናት፤ እናንተን ግን ከውስጧ አወጣችኋለሁ። 8ሰይፍን ፈርታችኋል፤ እኔም ሰይፍ እልክባችኋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9ከከተማዪቱ አውጥቼ ለባዕዳን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ ፍርድንም አመጣባችኋለሁ። 10በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤ በዚያ ጊዜም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 11ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፤ እናንተም በውስጧ ሥጋ አትሆኑም፤ በእስራኤልም ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤ 12በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እናንተ በዙሪያችሁ ያሉትን አሕዛብ ሥርዐት ተከተላችሁ እንጂ ትእዛዜን አልፈጸማችሁም ሕጌንም አልጠበቃችሁምና።”
13ትንቢት እየተናገርሁ ሳለ፣ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ተደፍቼ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ወዮ! የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን?” በማለት በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
14 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 15“የሰው ልጅ ሆይ፤ ወንድሞችህ፣ የራስህ ዘመዶችና#11፥15 ወይም በምርኮ ከአንተ ጋር የነበሩና (ሰብዐ ሊቃናትና ሱርስትን ይመ) የእስራኤል ቤት ሁሉ፤ ‘ከእግዚአብሔር ርቀዋል፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታናለች’ ብለው የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተናገሩባቸው ናቸው።#11፥15 ወይም የኢየሩሳሌም ሰዎች የተናገሩባቸው፣ ከእግዚአብሔር ራቁ
የእስራኤል የመመለስ ተስፋ
16“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በአሕዛብ መካከል ብሰድዳቸውም፤ በአገሮች መካከል ብበታትናቸውም፣ በሄዱባቸው አገሮች ሁሉ ለጥቂት ጊዜ መቅደስ ሆኜአቸዋለሁ’ ”።
17“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።’
18“ወደዚያ በተመለሱ ጊዜ የረከሱ ምስሎቿንና ጸያፍ ተግባሯን ያስወግዳሉ። 19የማያወላውል ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ አዲስ መንፈስ በውስጣቸው አኖራለሁ፤ ድንጋዩን ልብ ከውስጣቸው አወጣለሁ፤ ሥጋ ልብም እሰጣቸዋለሁ። 20ስለዚህ ትእዛዜን ይፈጽማሉ፤ ሕጌን ይጠብቃሉ። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ። 21ነገር ግን ልባቸው ወደ ረከሱ ምስሎቻቸውና ወደ ጸያፍ ተግባራቸው ያዘነበለውን እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
22ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፤ መንኰራኵሮቹም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበር። 23የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማዪቱ ውስጥ ተነሥቶ ወጣ፤ ከከተማዪቱም በስተ ምሥራቅ ካለው ተራራ በላይ ቆም አለ። 24መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፤ በእግዚአብሔርም መንፈስ በተሰጠው ራእይም በባቢሎን#11፥24 ወይም ከለዳውያን ምድር ወደ ነበሩት ምርኮኞች አመጣኝ።
ከዚያም ያየሁት ራእይ ከእኔ ወጥቶ ሄደ፤ 25እኔም እግዚአብሔር ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞቹ ተናገርሁ።
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 11: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.