ሕዝቅኤል 10
10
የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ ተለየ
1እኔም አየሁ፤ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ፣ የሰንፔር ዙፋን#10፥1 ወይም ላፒስላዙሉ የሚመስል ነገር ነበረ። 2እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “በኪሩቤል ሥር ወዳሉት መንኰራኵሮች መካከል ግባ፤ በኪሩቤል መካከል ካለውም የእሳት ፍም እጅህን ሞልተህ ዝገን፤ በከተማዪቱም ላይ በትነው” አለው። ሰውየውም እያየሁት ገባ።
3ሰውየው ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ፣ ኪሩቤል በቤተ መቅደሱ ውስጥ በደቡብ በኩል ቆመው ነበር፤ ደመናም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ። 4የእግዚአብሔርም ክብር ከነበረበት ከኪሩቤል በላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መድረክ ሄደ፤ ደመናው ቤተ መቅደሱን ሞላ፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ተሞላ። 5ሁሉን የሚገዛ#10፥5 ዕብራይስጡ ኤል-ሻዳይ ይለዋል አምላክ ሲናገር እንደሚሰማው ድምፅ ዐይነት፣ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጪው አደባባይ ድረስ ይሰማ ነበር።
6 እግዚአብሔር በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “ከኪሩቤል ዘንድ ከመንኰራኵሮቹ መካከል እሳት ውሰድ” ብሎ ባዘዘው ጊዜ፣ ሰውየው ወደ ውስጥ ገብቶ በአንዱ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ። 7ከኪሩቤልም አንዱ በመካከላቸው ወዳለው እሳት እጁን ዘርግቶ ጥቂት ወሰደ፤ በፍታ በለበሰው ሰው እጅ ላይ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ። 8ከኪሩቤል ክንፎች ሥር የሰው እጅ የሚመስል ይታይ ነበር።
9እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ በእያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ አንድ መንኰራኵር ነበር፤ የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ያንጸባርቅ ነበር። 10የአራቱም መልክ ይመሳሰል ነበር፤ እያንዳንዱም መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር። 11መንኰራኵሮቹ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜም ኪሩቤል ወደ ዞሩበት ወደ አራቱ አቅጣጫ ሁሉ መሄድ ይችሉ ነበር፤ ኪሩቤል በሚሄዱበት ጊዜ መንኰራኵሮቹ ወዲያ ወዲህ#10፥11 ወይም ወደ አንድ ወገን አይሉም ነበር አይሉም ነበር፤ ኪሩቤል በሚሄዱበት ጊዜ ወዲያ ወዲህ ሳይሉ፣ ራስ ወደ ዞረበት ወደ ማንኛውም አቅጣጫ ይጓዙ ነበር። 12ጀርባቸውን፣ እጃቸውን፣ ክንፋቸውን ጨምሮ መላ ሰውነታቸው እንዲሁም አራቱ መንኰራኵሮቻቸው በጠቅላላ በዐይን የተሞሉ ነበሩ። 13መንኰራኵሮቹም፣ “ተሽከርካሪ መንኰራኵሮች” ተብለው ሲጠሩ ሰማሁ። 14እያንዳንዱም ኪሩብ አራት አራት ፊት ነበሩት፤ ይኸውም አንደኛው ፊት የኪሩብ፣ ሁለተኛው የሰው ፊት፣ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፣ አራተኛውም የንስር ፊት ነበር።
15ኪሩቤልም ወደ ላይ ተነሡ፤ እነዚህም በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየኋቸው ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ። 16ኪሩቤል ሲንቀሳቀሱ፣ መንኰራኵሮቹም ከጐናቸው ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ኪሩቤልም ከምድር ለመነሣት ክንፋቸውን ሲዘረጉ፣ መንኰራኵሮቹ ከአጠገባቸው አይለዩም ነበር። 17ኪሩቤል ቀጥ ብለው በሚቆሙበት ጊዜ እነርሱም ደግሞ ይቆማሉ፤ ኪሩቤል ከምድር ከፍ ከፍ በሚሉበት ጊዜ፣ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ፣ መንኰራኵሮችም አብረዋቸው ይነሡ ነበር።
18ከዚህ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ ደጃፍ ላይ ተነሥቶ ከኪሩቤል በላይ ቆመ። 19ኪሩቤልም እኔ እያየኋቸው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ከምድር ተነሥተው ሄዱ፤ መንኰራኵሮቹም አብረዋቸው ሄዱ፤ በእግዚአብሔርም ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ላይ ቆሙ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበር።
20እነዚህ በኮቦር ወንዝ አጠገብ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ፤ ኪሩቤልም እንደ ሆኑ አስተዋልሁ። 21እያንዳንዳቸው አራት አራት ፊት፣ አራት አራት ክንፍ፣ ከክንፎቻቸውም ሥር የሰውን እጅ የሚመስል ነበራቸው። 22ፊታቸውም በኮቦር ወንዝ አጠገብ ካየኋቸው ጋር ይመሳሰል ነበር፤ እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 10: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.