ዘፀአት 5:15-23

ዘፀአት 5:15-23 NASV

ከዚያም ሥራውን በቅርብ ሆነው የሚቈጣጠሩት እስራኤላውያን ኀላፊዎች ፈርዖን ፊት ቀርበው እንዲህ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፤ “እኛን ባሮችህን እንደዚህ የምታደርገን ለምንድን ነው? ለእኛ ለባሮችህ ጭድ ሳያቀርቡልን ሸክላ ሥሩ ይሉናል፤ ጥፋቱ የገዛ ሰዎችህ ሆኖ ሳለ እኛ ባሮችህ ግን እንገረፋለን።” ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ልግመኞች! እናንተ ልግመኞች! እየደጋገማችሁ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔር እንሠዋ’ የምትሉት ለዚህ ነው። በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ፤ ምንም ጭድ አይሰጣችሁም፤ ያም ሆኖ ግን የተመደበላችሁን ሸክላ ማምረት አለባችሁ።” እስራኤላውያን ኀላፊዎችም፣ “በየቀኑ የምትሠሩት ሸክላ ቍጥሩ ቀድሞ ከሚሠራው ሸክላ ማነስ የለበትም” ተብሎ ሲነገራቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተረዱት። ከፈርዖን ዘንድ እንደ ተመለሱ ሲጠብቋቸው የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አግኝተው፣ “እግዚአብሔር ይይላችሁ፤ ይፍረድባችሁም፤ ፈርዖንና ሹማምቱ እንዲጠየፉን አደረጋችሁ፤ እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ ሰጣችኋቸው” አሏቸው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፣ “አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ ያመጣኸው ለምንድን ነው? የላክኸኝ ለዚሁ ነው? በአንተ ስም እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከሄድሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ አበሳ አምጥቷል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አልታደግኸውም” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}