ዘፀአት 5
5
ጭድ አልባ ሸክላ
1ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይላል” አሉት።
2ፈርዖንም “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ማነው? እግዚአብሔርን (ያህዌ) አላውቅም፤ እስራኤልንም አልለቅም” አለ።
3እነርሱም፣ “የዕብራውያን አምላክ (ኤሎሂም) ለእኛ ተገልጦልናል፤ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳው ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ አለዚያ ግን በመቅሠፍት ወይም በሰይፍ ይመታናል” አሉት።
4የግብፅ ንጉሥም፣ “እናንተ ሙሴና አሮን፤ ለምንድን ነው ሕዝቡን ሥራ የምታስፈቱት? በሉ እናንተም ወደየሥራችሁ ተመለሱ!” 5ፈርዖንም፣ “እነሆ፤ አሁን የምድሪቱ ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፤ እናንተም እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” አለ።
6በዚያኑ ዕለት ፈርዖን ለባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና ለሕዝቡ አለቆች እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ 7“ለጡብ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ጭድ ካለበት ቦታ ሄደው ራሳቸው ያምጡ እንጂ ከእንግዲህ እናንተ እንዳታቀርቡላቸው። 8ሆኖም ቀድሞ በሚያቀርቡት ሸክላ ልክ ሠርተው እንዲያቀርቡ አድርጓቸው። የሥራ ድርሻቸውን አትቀንሱ። ሰነፎች ናቸው፤ ‘ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት እንሠዋ’ የሚሉትም ለዚህ ነው። 9ለሐሰት ወሬ ስፍራ ሳይሰጡ ተግተው እንዲሠሩ ሥራውን አክብዱባቸው።”
10ከዚያም የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና አለቆቹ ወጥተው ለሕዝቡ፣ “ፈርዖን የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእንግዲህ ጭድ አልሰጣችሁም፤ 11ሂዱና የራሳችሁን ጭድ ከየትም ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራ ድርሻችሁ ግን ከቶ አይቀነስም’ ” አሉ። 12ስለዚህም ሕዝቡ በጭድ ፈንታ ገለባ ለመሰብሰብ በግብፅ ምድር ሁሉ ተሰማሩ።
13የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹም “በየዕለቱ መሥራት የሚገባችሁ ሥራ ቀድሞ ጭድ ስናቀርብላችሁ ከምትሠሩት ሥራ ማነስ የለበትም” እያሉ ያጣድፏቸው ነበር። 14የሥራው የቅርብ ኀላፊዎች ተደርገው በፈርዖን የባሪያ ተቈጣጣሪዎች የተመደቡት እስራኤላውያንም፣ “የትናንቱንም ሆነ የዛሬውን ሸክላ ሥራ ድርሻችሁን እንደ ቀድሞው ለምን አላሟላችሁም?” እየተባሉ ይጠየቁና ይገረፉ ነበር።
15ከዚያም ሥራውን በቅርብ ሆነው የሚቈጣጠሩት እስራኤላውያን ኀላፊዎች ፈርዖን ፊት ቀርበው እንዲህ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፤ “እኛን ባሮችህን እንደዚህ የምታደርገን ለምንድን ነው? 16ለእኛ ለባሮችህ ጭድ ሳያቀርቡልን ሸክላ ሥሩ ይሉናል፤ ጥፋቱ የገዛ ሰዎችህ ሆኖ ሳለ እኛ ባሮችህ ግን እንገረፋለን።”
17ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ልግመኞች! እናንተ ልግመኞች! እየደጋገማችሁ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንሠዋ’ የምትሉት ለዚህ ነው። 18በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ፤ ምንም ጭድ አይሰጣችሁም፤ ያም ሆኖ ግን የተመደበላችሁን ሸክላ ማምረት አለባችሁ።”
19እስራኤላውያን ኀላፊዎችም፣ “በየቀኑ የምትሠሩት ሸክላ ቍጥሩ ቀድሞ ከሚሠራው ሸክላ ማነስ የለበትም” ተብሎ ሲነገራቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተረዱት። 20ከፈርዖን ዘንድ እንደ ተመለሱ ሲጠብቋቸው የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አግኝተው፣ 21“እግዚአብሔር (ያህዌ) ይይላችሁ፤ ይፍረድባችሁም፤ ፈርዖንና ሹማምቱ እንዲጠየፉን አደረጋችሁ፤ እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ ሰጣችኋቸው” አሏቸው።
እግዚአብሔር እንደሚታደግ ተስፋ ሰጠ
22ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተመልሶ፣ “አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ ያመጣኸው ለምንድን ነው? የላክኸኝ ለዚሁ ነው? 23በአንተ ስም እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከሄድሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ አበሳ አምጥቷል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አልታደግኸውም” አለው።
Currently Selected:
ዘፀአት 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.