የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 3:1-20

ዘፀአት 3:1-20 NASV

አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የአማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ። እዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለ መቃጠሉን አየ። ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ። ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው፤ ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው። ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፣ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ። ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ። አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ። በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”። ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ታመልካላችሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ (ያህዌ)፤ ስለዚህም፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው። ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው። “ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብፅ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ። ስለዚህም በግብፅ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ። “የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ። የግብፅ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በስተቀር መቼም እንደማይለቅቃችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብፃውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቃችኋል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}