ዘዳግም 14:22-29

ዘዳግም 14:22-29 NASV

በየዓመቱ ከዕርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ። ምን ጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላ። ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ባርኮህ ሳለ፣ መንገዱ ቢርቅብህና እግዚአብሔር የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ ዐሥራትህን ወደዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልህ፣ ዐሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ፣ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ። የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው፣ በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው። በየሦስት ዓመቱ መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል ዐሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች። ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።