ዘዳግም 14:22-29
ዘዳግም 14:22-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከእርሻህ ዘርተህ በየዓመቱ ከምታገኘው እህልህ ሁሉ ዐሥራት ታወጣለህ። በዘመንህም ሁሉ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራትን ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን፥ የወይንህን፥ የዘይትህንም ዐሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ። አምላክህ እግዚአብሔር ባርኮሃልና፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ በብር ትሸጠዋለህ፤ ብሩንም በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ። በዚያም በብሩ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ብርቱ መጠጥ፥ ሰውነትህ የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፤ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል። ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በከተማህ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል። “በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን ዐሥራት ሁሉ አምጥተህ በከተማዎችህ ውስጥ ታኖረዋለህ። ሌዋዊዉም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በከተማህ ውስጥ ያለ መጻተኛ፥ ድሃ-አደግም፥ መበለትም መጥተው ይበላሉ፤ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።
ዘዳግም 14:22-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በየዓመቱ ከዕርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ። ምን ጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላ። ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ባርኮህ ሳለ፣ መንገዱ ቢርቅብህና እግዚአብሔር የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ ዐሥራትህን ወደዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልህ፣ ዐሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ፣ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ። የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው፣ በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው። በየሦስት ዓመቱ መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል ዐሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች። ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።
ዘዳግም 14:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእርሻህ በየዓመቱ ከምታገኘው ከዘርህ ፍሬ ሁሉ አሥራት ታወጣለህ። ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን የወይን ጠጅህንም የዘይትህንም አሥራት የላምህንና የበግህንም በኩራት ብላ። አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ ትሸጠዋለህ፥ የዋጋውንም ገንዘብ በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ። በዚያም በገንዘቡ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ ወይም የወይን ጠጅ ወይም ብርቱ መጠጥ ሰውነትህም የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፥ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል። ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በአገርህ ደጅ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል። በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን አሥራት ሁሉ አምጥተህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ታኖረዋለህ፤ ሌዋዊውም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በአገርህም ደጅ ያለ መጻተኛ ድሀ አደግም መበለትም መጥተው ይበላሉ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።
ዘዳግም 14:22-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“በየዓመቱ አርሰህ ከምታገኘው ሰብል ሁሉ ከዐሥር እንዱን እጅ ለይተህ ታስቀምጣለህ፤ ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ቦታ የእህልህን፥ የወይን ጠጅህን፥ የዘይትህን ዐሥራት፥ እንዲሁም የከብቶችህንና የበጎችህን በኲራት በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላለህ፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ እርሱ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን የመረጠው ቦታ ከአንተ በጣም ሩቅ በመሆኑ ለይተህ ያስቀመጥከውን ዐሥራት ለማጓጓዝ ቢያስቸግርህ፥ ዐሥራቱን ሸጠህ ገንዘቡን በመያዝ እግዚአብሔር እንዲመለክበት ወደ መረጠው ቦታ ሂድ። እዚያም በገንዘቡ የምተፈልገውን ነገር ከብት፥ ወይም በግ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ጠንካራ መጠጥ፥ ወይም ማንኛውንም የመረጥከውን ነገር ገዝተህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አንተና ቤተሰብህ በመብላት ተደሰቱ። “በከተሞችህ የሚኖሩ ሌዋውያን ድርሻ ወይም ርስት ስለሌላቸው እነርሱን ችላ አትበል። በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ከእርሻችሁ ሰብል ሁሉ ከዐሥር አንዱን እያወጣችሁ በከተሞቻችሁ አከማቹ፤ በከተሞቻችሁ የሚኖሩ ከእናንተ ጋር የተካፈሉት ርስት የሌላቸው ሌዋውያን፥ የውጪ አገር ስደተኞች፥ እናትና አባት የሌላቸው የሙት ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መጥተው ይብሉ፤ ይህን ሁሉ ብታደርጉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምትሠሩት ነገር ሁሉ ይባርካችኋል።
ዘዳግም 14:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በየዓመቱ ከእርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ። ምንጊዜም ጌታ እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፥ የወይን ጠጅና የዘይትህን አሥራት፥ የቀንድ ከብትህን፥ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፥ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ትበላለህ። ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ፥ መንገዱ ቢርቅብህና ጌታ አምላክህ የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ አሥራትህን ወደ እዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልክ፥ አሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ ጌታ አምላክህ ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ ማለትም በሬና በግ፥ የወይን ወይም የብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተሰብህ በጌታህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፤ አንተና ቤተሰብህም ሐሤትም ታደርጋላችሁ። በከተሞችህ የሚኖሩ ሌዋውያን ድርሻ ወይም ርስት ስለ ሌላቸው እነርሱን ችላ አትበል። “በየሦስት ዓመቱም መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል አሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች። ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፥ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፥ አንተንም አምላክህ ጌታ በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።