ሐዋርያት ሥራ 7:51-60

ሐዋርያት ሥራ 7:51-60 NASV

“እናንተ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ! ዐንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ። ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤ በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።” በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣ “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሯቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤ ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጕልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ። እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት፤” ብሎ ጸለየ፤ ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው!” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ።